በሰላም ወቅት በጠመኔ፣ በጦርነት ወቅት በጦር መሳሪያ

176

ታኅሣሥ 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝን ከጀርባው ወግቶ የፈጸመው ክህደት ኢትዮጵያውያንን እጅግ ያሳዘነ እና ያስቆጣ ክስተት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ክህደት እና ባንዳነት የሽብር ቡድኑ ተወልዶ ያደገበት ባሕሪው ቢሆንም በዚህ ልክ የኔ የሚለውን ሕዝብ ሲጠብቅ እና ሲንከባከብ የነበረን ሰራዊት ይዳፈራል ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡ አሸባሪው ቡድንም ውልደቱ ለጥፋትና ሀገር ለማፍረስ ነውና አደረገው፤ በምላሹም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ ጫፍ በአንድነት ተነስቶ ይህንን አረመኔ አሸባሪ የትግራይ ወራሪ ቡድን አይቀጡ ቅጣት ቀጣው፡፡
እንደ ሀገር አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን ለመቅጣት በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በየሚዲያው እየወጣ ክህደቱን እንደ ጀብድ፣ ነውሩን እንደ ጌጥ፣ ዘራፊነቱን እንደ ሙያ፣ አረመኔነቱን እንደ መልካም ሲገልጽ እና ሲያቅራራ የነበረው በሁለት ሳምንታት ብቻ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ተደቁሶ ደብዛው ጠፋ፡፡ “አጉል እዩኝ እዩኝ፣ ደብቁኝ ደብቁኝ ያመጣል” እንዲሉ አበው መግቢያ ጉድጓድ አስኪጠፋው ድረስ ተቀጠቀጠ፡፡ ኢትዮጵያን ያህል ታላቅ ሀገር እበትናለሁ ብሎ ሲያስብ በኢትዮጵያውያን ተዋረደ፡፡

ይህ አልበቃ ብሎት ያለ የሌለ ኀይሉን አሰባስቦ የአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ በመፈጸም የተሸናፊነት እና የሞራል ውድቀቱን ንጹሃን ወገኖችን በመጨፍጨፍ፣ በመዝረፍ፣ በመድፈር እና በማሰቃየት አሳየ፡፡ የቀረውን እና እንደ ሰው በሰላም መኖር ያልተቻለውን አሸባሪ የትግራይ ወራሪ ቡድንም ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከያሉበት በድጋሜ ተጠራርተው ተነሱ፤ አመርቂ ድልም እየተቀዳጀ ነው፤ የሚደመሰሰው ተደምስሶ ማምለጫ ያጣው እና ማንም እንደማያስጥለው ያወቀው እየተሯሯጠ እና መጠጊያ እየፈለገ ነው፡፡
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን በዳግም ክህደት የአፋር እና አማራ ክልሎችን ሲወር ካጠፋው ሕይወት እና ከዘረፈው ብሎም ካወደመው ንብረት መካከል ተማሪዎች፣ መምህራን እና ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል፡፡ የተማሪዎቻቸውን መገደል፣ መፈናቀል እና መደፈር ብሎም የትምህርት ቤቶቻቸው መውደም ያንገበገባቸው መምህራንም ከሰራዊቱ ጋር ግንባር ድረስ ዘምተው አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን አይቀጡ ቅጣት እየቀጡ ነው፡፡
በግንባር ከሰራዊቱ ጋር ያገኘናቸው መምህራን እንደገለጹት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ዳግም የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ስጋት እና የቤት ሥራ እንዳይሆን የመቅበር ዘመቻ ውስጥ በመሳተፋቸው ደስታቸው ወደር የለውም፡፡ በአዲአርቃይ ወረዳ የትምህርት ቤት ርእሰ መምህር እንደነበሩ የነገሩን አስምሮ መንግሥቱ ከደደቢት ዋሻ ጀምሮ አማራን የማጥፋት እና ኢትዮጵያን የመበተን ቅዠት ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በፈጸመው ወረራ በርካታ ውድመቶችን መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ እናም እርሳቸው ሲያስተምሩአቸው የነበሩ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ወላጆቻቸም በሽብር ቡድኑ ተገድለዋል፤ ተደፍረዋል፤ ከሽብር ቡድኑ ጥቃት የተረፍትም ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ፡፡
እናም ይህ አረመኔ ቡድን እያለ ማንም በሰላም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማድረግ ቀርቶ ለህልውናውም አስጊ በመሆኑ ከሰራዊቱ ጋር ባልደረቦቻቸውን ይዘው መዝመታቸውን ተናግረዋል፡፡ ርእሰ መምህሩ ይህ የሀገር ጠንቅ የሆነ አሸባሪ የትግራይ ወራሪ ቡድንን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍና ደጀን በመሆን ሥንቅ እና ትጥቅ በማቅረብ ኀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ፋኖ፣ ሚሊሻ እና ሕዝባዊ ሰራዊቱ እየፈጸሙት ያለው ጀብድ እጅግ የሚያኮራ መሆኑን የገለጹት ርእሰ መምህሩ ከእነዚህ የሀገር ጀግኖች ጎን መሰለፍና ታሪክ መሥራት ኩራት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን እያለ ተማሪ፣ መምህር፣ ትምህርት፣ ትምህርት ቤት ብሎም ሀገር የሚባል ነገር ስለማይኖር ሁሉም ዘመቻውን መቀላቀላቸውን ገልጸዋል፡፡ ውርደት እና ሽንፈት እየተከናነበ ያለው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን እስኪደመሰስ እና ሀገር እና ሕዝብ ነጻ እስኪወጡ እንደሚፋለሙም አረጋግጠዋል፡፡
ሦስት ወንድሞቻቸውን ጭምር አበረታተው እና መርቀው ወደ ዘመቻ መላካቸውን የተናገሩት መምህርት እናኑ ደሞዜ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በዋልድባ ለሚኖሩ መነኮሳት እንኳ ያልራራ አረመኔ ቡድን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ንጹሃንን ሲገድል፣ ሲደፍር፣ ሲያፈናቅል እና ሲዘርፍ በማየታቸው እርሳቸውም ይህንን አረመኔ ቡድን ለማጥፋት በሚደረገው የሕልውና ዘመቻ እየተሳተፍ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በግንባር ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍም ስንቅ እና ትጥቅ እስከ ምሽግ ድረስ በማድረስ አጋርነታቸውን እያሳዩ እንደሆነ መምህርቷ ተናግረዋል፡፡

በሰላሙ ወቅት በጠመኔ መሃይምነትን ሲዋጋ የነበረው መምህሩ ሀገር ችግር በገጠማት ወቅት የጦር መሳሪያ ይዞ ጠላትን መደምሰስ ግድ ይለዋል ያሉት መምህርት እናኑ እርሳቸው እና ባልደረቦቻቸውም ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡ እናም ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ተደምስሶ የተፈናቀሉ ተማሪዎቻቸው ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው፣ የትምህርት ተቋማቱ ታድሰው ሥራ የሚጀምሩበት ቀንን በመናፈቅ እየተፋለሙ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ግንባር ያገኘናቸው ሌላኛው መምህር አበበ ፈንቴ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን በፈጸመው ወረራ የመማር ማስተማር ሂደቱ መደናቀፉን ገልጸው ይህንን አረመኔ ቡድን በመደምሰስ ሀገርን እንዴት ከጠላት መጠበቅ እንደሚገባ በተግባር ለማስተማር ጭምር መዝመታቸውን ተናግረዋል፡፡ መምህራን ለሰራዊቱ ስንቅ እና ትጥቅ በማቅረብ፣ አካባቢን በመጠበቅ እና ሰርጎ ገቦችን በመያዝ በህልውና ዘመቻው የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ለማንም ለምንም የማይበጅ ጠላት በመሆኑ በአንድነት ልናጠፋው ይገባልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡-የማነብርሃን ጌታቸው
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ!!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

Previous articleየአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ከአዲስ አበባ የተሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ሠራተኞች ማኅበር ጋር በመተባበር ለወልድያ ከተማ ነዋሪዎች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ ድጋፍ አደረገ።
Next article“ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የምንመለከትበት መነጸር ሊቀየር ይገባል” ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት