
ታኅሣሥ 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ ወቅታዊ መግለጫ በባሕር ዳር ከተማ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የኅልውና ዘመቻ በተሳካ ሁኔታ እየተገባደደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ስኬቱን አጣምመው ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያሠራጩ ትላልቅ መገናኛ ብዙኀኖች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ መገናኛ ብዙኀኖች የተሸነፈውን አሸባሪ ቡድን እንዳልተሸነፈ በመቁጠር አሁንም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ታሪክን አጣምሞ ማቅረባቸውን ቀጥለውበታል ነው ያሉት፡፡
አምባሳደር ዲና በግንባር የጸጥታ ኀይሎች ጥምረት ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ በርካታ ድሎችን አስመዝግቧል ብለዋል፡፡ በዚያው ልክ አሸባሪው ቡድን በርካታ ጉዳቶችን በሕዝብ ላይ ማድረሱን ነው የገለጹት፡፡ ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀኖች ሐቁን ደብቀው አድሏዊ አሠራር እየተከተሉ ነው ብለዋል። የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ይህንን የተዛባ የመረጃ ዘመቻ ማጋለጥና መቀልበስ እንደሚጠበቅባቸውም አመላክተዋል፡፡
የሐሰት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎችን በተደራጀ አግባብ ማጋለጥ ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደሩ ነገ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በሀገሪቱ ላይ እየተካሄደ ያለውን የተዛባ ትርክት ለማስተካከልና የተዛባ የመረጃ ዘመቻውን ለማክሸፍ ያለመ ፎረም እንደሚያካሂድ ገልጸዋል፡፡ በፎረሙ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ ይህም የትምሕርት ተቋማት በፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ በገጽታ ግንባታ እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሀገር ኅልውና ጋር በተሳሰረ መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጪ ግንኙነቷን ማሳለጥ የምትችልበት እድል አግኝታለች፡፡ አፍሪካውያንን ከጎኗ ማሰለፍ እንደቻለችም አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራትም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ጉዳይ ከ10 ጊዜ በላይ ያቀረቡ ሀገራት እንዳይሳካላቸው አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይን አጣምሞ ለማቅረብ ያደረጉት ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል ብለዋል፡፡
አሁንም የተሸነፈውን ኀይል ኅልውና እንዳለው አስመስሎ የማቅረብና ነፍስ የመዝራት አቅጣጫ እየተከተሉ መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያውያን ይህንን እስከመጨረሻ የመመከት ሥራ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ወዳጅ ዜጎች ጋር የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል ወደ ሀገር ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑም በተመለከተ በመግለጫው አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን እና ወዳጅ ሀገራት ዜጎች መግባት እንደጀመሩ ነው በመግለጫው የገለጹት፡፡
ዲያስፖራው ወደ ሀገር መግባት ከወገኑ ጎን እንዲቆም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለውን ያልተገባ ጫና ለመቀልበስና የበቃ ንቅናቄን ለማፋፋም እንደሚያግዝ አንስተዋል፡፡
ዲያስፖራው በተለያዩ መስኮች ትልቅ አቅምና ልዩ ልዩ ችሎታ ያሉት በመሆኑ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ወደሙትን መልሶ በመገንባት ሂደቱ ሚናቸው ጉልህ እንደሚሆን ጠቅሰዋል። ቱሪዝም በመሳብ፣ ተስማሚ ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር በማስገባት፣ ንግድን በማጠናከርና በመሳሰሉት ተግባራት ትልቅ ሚና ይጫወታሉም ብለዋል፡፡ ይህንን ለማመቻቸት ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥሩ ሥራ እያከናወነ ሲሆን ላል ይበላ እና ጎንደርን ጨምሮ በሀገሪቱ ታሪካዊ ቦታዎች ልዩ ልዩ ኹነቶች እንደሚዘጋጁም አመላክተዋል፡፡
ብሔራዊ ውይይትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በሀገሪቱ ውስጥ የሚታዩትን አለመግባባት ለመፍታት የሚቻልበት ሀገር አቀፍ ምክክር እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል። ውይይቱ ልዩነቶችን ሰላማዊ ለማድረግ ያለመ ሲሆን በሁሉም ኢትዮጵያውያን መካከል የሚደረግ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ብሔራዊ ውይይቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከፈረጀው ቡድን ጋር የሚደረግ ድርድር እንዳልሆነ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
