“ቢጫ በለበሱት እማሆይ ውስጥ ኢትዮጵያን እና እውነትን አየኋቸው”

240

ታኅሣሥ 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሐምሌ ሰማይ ከብዷል፣ ደመና በከበደው ሰማይ ላይ ጉርምርምታው አስደንጋጭ ሆኗል። የደጋው ቆፈን አሳስሮ ይጥላል፣ ብርዱ ይቆራርጣል፣ በተራራው ጫፍ ላይ ሲጎተት የነበረው ጉም ከተራራው ወርዶ በሜዳውም እየተጎተተ ነው። ከደመናው ጋር የሚመጣው ቀዝቃዛ አየር የት በገባሁ ያሰኛል። በቀን የጨለመ ይመስላል። አሻግሮ ጋራውን መመልከት አይቻልም ነበር። ቀኑ የሚያልፍ ብርሃንም የሚመጣ አይመስልም። ሰማይና ምድር የተገናኙ፣ ፀሐይም ለዘለዓለም የጠለቀች ትመስላለች፣ ዘመን ተፈፅሞ ይሆን? ያስብላል።
ሰማይ ዝቅ ብሎ ምድርን የተጫነው ይመስላል፣ የቀን ጨለማ የሚሉት ቀን። በዚህ አስቸጋሪ ቀን ወገባቸው በትጥቅ የተሞላ ጀግኖች በምሽጋቸው ተቀምጠዋል። ለሕዝብ ፍቅር፣ ለሀገር ክብር ሲሉ ያን አስቸጋሪ ብርድ ረስተውታል። የእነርሱ ትኩረት ብርዱ ላይ አልነበረም። እነርሱ ሌሎች በሞቀ ቤት እንዲኖሩ፣ በተደላደለ መኝታ ላይ እንዲያድሩ ነበር ቆፈን በበዛበት የቀን ጨለማ ምሽግ ውስጥ የተቀመጡት። አካባቢን እየወረረ፣ ቀዬን እየደፈረ፣ አድባር እያረከሰ፣ ሀብት እያወደመና እየዘረፈ፣ እሴትና ታሪክ እያፈረሰ የሚመጣ ቡድን ነበርና ያን ቡድን ይመቱ ዘንድ ነበር እኒያ ጀግኖች በዚያ ብርዳም ቀን በምሽግ መቀመጣቸው። ብርዱ ተረስቶ ደም የሚቀዳበት፣ አጥንት የሚሰበርበት፣ ሕይወት የሚገበርበት ጦርነት ሊጀመር ነው።
ጀግኖቹ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው በተጠንቀቅ ላይ ናቸው። ጠላት ወደ ምሽጋቸው አቅጣጫ እየጎረፈ ነው። “በለው” የሚል ትዕዛዝ አዛዣቸው አስተላለፉ። የተዘጋጀው ጥይት አውካካ፣ አካባቢው በጥይት ታመሰ። በሰማይ ጉርምርምታው በምድር የጥይት እሩምታው ተቀላቅሎ ዓለም ልታልፍ ትመስላለች። የማያቋርጥ ተኩስ ተተኮሰ፣ ጀግኖች እያለሙ ይነጥሉታል። በሕዝብ ማዕበል የሚመጣው ጠላት በጀግኖቹ ጥይት እየተመነጠረ ይወድቃል። ጥይታቸው ዝም ብላ አትወድቅም። ሰው እየያዘች እንጂ። ጠላት እንደ ቅጠል ረገፈ። ጀግኖቹ በያዙት ጥይት ልክ ሰው ይጥላሉ። ጠላትም ይረግፋል። ምድር በጥይት እየታረሰች፣ ደም እየተቀዳ፣ ሰዓታት አለፉ። ገና በእኩለ ቀን የጨለማው ብርዳም ቀን እየመሸ ነው። መምሸቱን ማወቅ የሚቻለው የእጅ ሰዓት ተመልክቶ እንጂ የጀንበርን አወራረድ ተመልክቶ አልነበረም። ጀንበር ከጠቆረው ደመና ውስጥ ተሰንጋ ከቀረች ቆይታለች እና። ዳግም የምትዘልቅም አትመስልም።
ቀኑ እየመሸ ሄደ። ይባስ ብሎ ሲጎተት የነበረው ደመና ዝናብ ያወርድ ጀመር። ጥይት እየተተኮሰባቸው፣ ዝናብ እየወረደባቸው፣ ምሽጋቸው በጎርፍ እየሞላባቸው ንቅንቅ የማይሉት ጀግኖቹ የአማራ ልዩ ኀይሎች ከጠላት ግንባር ላይ ደም ማፍለቃቸውን ቀጥለዋል። ከፊት ለፊታቸው ጠላት እየታጨደ ነው። አንደኛው መንጋ ሲያልቅ ሌላ መንጋ ለሞት ይቀርባል። ያን መንጋም ይጨርሱታል። ሌላ መንጋ ይጨምራል። ያንም እንዳልነበር ያደርጉታል። ምድሯ በዋይታ ተሞላች፣ ከጠላት ሰፈር አንሱኝ ደግፉኝ የሚለው በዝቷል።

አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን አዛዦች አንደኛው ሲያልቅ ሌላኛውን ለጥይት እያቀረቡ ያስደበድቡታል። ዓልሞ መሳት ነውር ነው የሚለው የጀግኖች መገኛ የአማራ ልዩ ኀይልም እየመጣ የሚሰበሰብለትን ጠላት ይወቀዋል። ሰዓታት አለፉ፣ ሰው ሳይሞትባት ያለፈች ደቂቃ አልነበረችም። ጠላት እየረገፈ ነው። ሰዓቱም እየነጎደ ነው። ጠላት እኒያን ጀግኖች ተራምዶ ማለፍ እንደማይሳካለት ገብቶታል። መንጋው እያለቀበት ነውና። ተጨማሪ የሕዝብ ማዕበል ጨምሮ በተለያዩ አቅጣጫዎች ጎረፈ። በዚህ ወቅት የጀግኖቹ አዛዥ አንድ ስልት መቀየስ ነበረባቸው። ልጆቻቸው ከነበሩበት ቦታ ለቅቀው ሌላ ቦታ እንዲይዙ ማድረግ። ትዕዛዝ ተሰጣቸው፣ የነበሩበትን ቦታ ትተው ሌላ ቦታ ያዙ። ታዲያ በዚህ ጊዜ ከምሽግ ወደ ምሽግ ሊዘዋወሩ ሲነሱ ከጀግኖች መካከል አንደኛው ጀግና በጥይት ተመትቶ ወደቀ። ቀኑ እየመሸ ነው። ከጠላት ጋር የነበረው ትንቅንቅ ቀጥሏል። ጀግኖቹ ቦታ ቀይረው መንጋውን እያረገፉት ነው። ያ ጀግና ግን በዚያው እንደወደቀ ነበር። ደም እየፈሰሰው ነው። ሰዓቱ መሽቷል። ዝናቡ አይሏል። አስቀድሞ ሌሊት ለመሆን የተዘጋጀው ቀን ድንግዝግዝ አለ። ጀንበርም አንድ ጊዜ እንኳን ሳትታይ በዚያው ነበር ቀልጣ የቀረችው። ሌሊቱን ሙሉ ዝናብ ሳያቋርጥ አደረ። ያ ጀግናም በዝናብ እየተመታ፣ ብርድ በበዛበት ሌሊት በዚያው አደረ። ደም በብዛት ፈስሶት ነበርና ሲነጋም ከጀግኖቹ ጋር መገናኘት አልቻለም። በዚያው ጋደም እንዳለ ጠላት ደረሰበት። ይህ ሥፍራ ቀበሮ ሜዳ ይሰኛል። በዚህ አውደ ውጊያ ጠላት ያለቀበትን የሰው ኀይል እናቱ ትቁጠረው እንጂ ማን ቆጥሮ ይጨርሳል ይላሉ። እንደ ቅጠል ረግፏል፣ እንደ አሸዋ ተበትኗልና። ጀግናው በጠላት እጅ ወደቀ። እንዳገኙት መግደል አልፈለጉም። ተሰቃይቶ እንዲሞት ፈረዱበት።
የወረሃ ሐምሌ ብርድ አይሏል፡፡ በደም መፍሰስ እና በረሃብ የተጎዳው ጀግናው ደክሟል። የእስታይሽ ከተማ ነዋሪዎች ያን ለእነርሱ ሲል ደሙን ያፈሰሰ ጀግና ተመለከቱት። ወዲያው እንዳያነሱት ሰግተዋል። ለአንድ ታላቅ አባትም ነገሯቸው። ጥበቡ ጉቼ ይባላሉ። ለሀገር ሲል የወደቀውን ጀግና አሰቡት። ለእኔ ሲል የወደቀውን ጀግና በቤቴ አስቀምጠዋለሁ እንጂ ዝም አልልም ብለው ከወደቀበት አንስተው ወደ ቤታቸው ወሰዱት። ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው የወራሪውን ቡድን ጥቃት ሸሽተው ነበርና በቤት ከእርሳቸው ውጭ ሌላ ሰው አልነበረም። ለመንከባከብ አስቸጋሪ ነበር። ግን ደሙን አጠቡለት። ቤት ያፈራውን አቀረቡለት። በእርሳቸው ቤት ውስጥ እንዳለ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑ አንድ ታላቅ ካሕን ሰሙ። እኒያ ካሕንም በእለተ ሰንበት ከቅዳሴ በኋላ በቤተክርስቲያን አፀድ ውስጥ ለተሰበሰቡ አማኞች አንድ ጀግና ለእኛ ሲል ወድቋል፣ በጥበቡ ጉቼ ቤትም አለ። ምግብ መብላት ስለማይችል የሚጠጣ እየያዛችሁ እንድትጠይቁት ሲሉ መልዕክት አስተላለፉ። አማኞችም የተባሉትን አደረጉ። ያላቸውን እየያዙ ይጠይቁት ጀመር። በዚህ ጊዜ የሀገር አድባር፣ ዋርካ፣ መልካም እናት፣ ለተቸገሩት ደራሽ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር ያለባቸው እየተባሉ የሚጠሩ አንዲት ደገኛ እናት አገኙት።
እማሆይ አበበች ላቀው ይባላሉ። አንደበታቸው ለምስጋና እና እውነትን ለመመስከር ብቻ ነው የሚከፈተው ይሏቸዋል። ደብር ሰሪ፣ ለእውነት ኗሪ፣ ለፍትሕ ተከራካሪ ናቸው ይሏቸዋል። ዋሾ ሰው አይቀርባቸውም፣ ክፉ ሰው አይጠጋቸውም ነው የሚባሉት። ወተት ይዘው ጠየቁት። ድሮም ማዘን ያውቁበታልና እንጀታቸው ተላወሰ። ባዩት ቀን እንቅልፍ ባይናቸው ሳይዞር አደረ። እናቱን እያሰቡ የልጁን ሕመም እያስታወሱ እንባ እያጠመቃቸው፣ አንጄታቸው እየተንሰፈሰፈ ሌሊቱን አሳለፉት። በማግሥቱም አጥሚት ይዘው ሊጠይቁት አቀኑ። በዚያ ቀን ግን ጥለውት ወደ ቤታቸው መሄድን አልመረጡም። ከጥበቡ ቤት አውጥተው ወደ እሳቸው ቤት መውሰድ ፈለጉ። ጥበቡ ብቻቸውን ነበሩና ለማስታመም ይቸገራሉ። እማሆይ ወደ ቤታቸው ይዘውት ሄዱ። ላም ነበረቻቸው ወተቷን ለእርሱ አደረጉ። ቁስሉንም በጨው እያጠቡ ይንከባከቡት ጀመር።
ቀናት ቀናትን እየተኩ፣ ሳምንታት ተተኩ፣ ሳምንታት ተተካክተው ወራት መጡ። ይሞታል ተብሎ የተፈራው ጀግና ተረፈ። ጠላቶቹም የት እንደገባ አላወቁም። በጭንቅ ቀን መልካም እናት አግኝቶ ለወራት ኖረ። አካባቢውም ከትግራይ ወራሪ ቡድን በወረሃ ታኅሣሥ ነፃ ወጣ።
ከአሚኮ ጋዜጠኞች ጋር የተገናኘው ድኖ ነበር። ተዋወቅን፣ ግርማ ገበየ ይባላል። ወደ እማሆይ ቤት ይወስደን ዘንድ ጠየቅነው። ይዞንም ሄደ። ከእርሳቸው ጋር ከተለያየ አንድ ሳምንት ሆኖት ነበር። ላል ይበላ ነፃ ስለ ወጣ ከጓደኞቹ ጋር ሊገናኝ በእግሩ ወደ ላል ይበላ ሄዶ ነበር። የሽብር ቡድኑ ሽሽት ላይ ስለ ነበረ በእስታይሽ ከተማ ቤት ለቤት እየገቡ ወገኖችን እንደሚገሉ መረጃው ደርሶት ነበር። ግርማም ከመከራ ያተረፉትን እናት ልዩ ኀይል አስጠልለሻል ተብለው እንዳይገደሉ ስለሰጋ ተደብቆ መውጣት መርጧል። እሳቸው ግን አብረን እንሞታለን እንጂ አይሆንም አሉ። የሆነው ሆነና የግርማ ሀሳብ አሸናፊ ሆነ። እሳቸውም እንባ እየተናነቃቸው ከጎረቤት፣ ከከተማው ወጣቶች ብር ጠያይቀው የእሳቸውንም ጨምረው ብር ሰጥተው ሸኙት። እርሱም ወደ ላል ይበላ አቀና። መንገድ ላይ አግኝተው ይገድሉት ይሆን እያሉ ሀሳቡ አባዝኗቸው ነበር።
እኛን ይዞን ሲሄድ፣ ሲያዩት ደስታቸው ወደር አልነበረውም። “ግርማዬ ለፍቼ እንዳለፋሁ እንዲቀን ሊወጣ ጥለኸኝ ስትሄድ እኮ አስጨንቀኸኝ ነበር። እዚህ ወጥተህ ሄደህ ልትሞትብኝ ነበር እኮ?” አሉት። “ምን ላድርግ እርሰዎን ከሚገድሉብኝ ብዬ እኮ ነው። እኔንም ካገኙኝ ይገድሉኛል። ቤት ውስጥ ከምሞት በበረሃ ልሙት ብዬም ነው” አላቸው። “ሞት አይቀርልኝ ልጄ፤ አብረን እንሞታለን እንጅ። አንተ እኮ መድኃኔዓለም ያመጣልኝ ልጄ እኮ ነህ” አሉት፡፡
እናትና ልጅ ሆነዋል። ያስቀናሉ። ተነፋፍቀዋል። በእናትና ልጁ የቃላት ልውውጥ ተገርሜ እመለከታቸዋለሁ። በእማሆይ ቤት ውስጥ ቁጭ ብለን ስላሳለፉት ጊዜ ማውጋት ጀመርን። እማሆይ ጉሩም እናት፣ ኢትዮጵያን ቢጫ በለበሱት መልካም መነኩሴ አየኋት፣ ኢትዮጵያን ከአንደበታቸው መልካም ብቻ በሚወጣው እናት ተመለከትኳት፣ ደግነት የበዛላቸው፣ መልካምነት የመላባቸው፣ እናት ናቸው። የፈጣሪ ፀጋ የበዛላቸው፣ በረከት የማይርቃቸው፣ ቅዱስ መንፈስ የሚጠብቃቸው ኢትዮጵያ ማለት እሳቸው ናቸው። እውነትንም ቢጫ በለበሱት መነኩሴ አየኋት፣ ኢትዮጵያዊነትን በላያቸው ተመለከትኳት። እሳቸው የደግነት እናት ናቸውና። “ልጆቼ መድኃኔዓለም አስተምሮናል” አሉን እማሆይ በቤታቸው ተቀምጠን ሳለ። እውነት ነው ብዙ ነገር አስተምሮናል። “ወታደሮቹ በመንገድ ሲያልፉ አሳዘኑኝ፣ ኑ ወደ ቤት አልላቸው፣ አልዘልቃቸው” የወገን ጦር አካባቢውን እያፀዳ ሲሄድ ነበር እሳቸው አይተው ማዘናቸው። ግሩም ልብ። ልክ የሌለው ማዘን። ጠላት ግርማ የት እንደደረሰ አላወቀም። ደክሞ ስለነበር ሞቷል ብሎ አስቧል። ማንም ሰው ግርማ በእማሆይ ቤት ውስጥ እንዳለ እንዳይናገር ተብሏል። መዳኑን ከሰሙ ይገድሉታል እና መኖሩ እንዳይሰማ ሁሌም የእማሆይ ስጋት ነው።
ግርማ ያን ቀን ያስታውሰው ጀመር። “ወራሪው ቡድን ወረራ እንደጀመረ ሰሜን ሸዋ ምንጃር አረርቲ ነበርን። ለሌላ ግዳጅ ወደ ኮረም እንድንገባ ተደረገ። በዚያ ቆይተን በድልብ አድርጎ ጠላት ገባ ሲባል ወደ ቀበሮ ሜዳ ሄድን። ሐምሌ 24 በቀበሮ ሜዳ ውጊያ አደረግን። የሕዝብ ማዕበል ይዞ መጣ። ተኩሳቸው ምንም አይደለም። አይችሉም። ግን ማዕበል ስለሆነ አንደኛውን ስትጥለው ሌላ ይመጣል። እየተነባበረ ይመጣል። እንጥለዋለን። ይመጣል። እንጨርሰዋለን ይተካል። ቦታ መቀየር ግድ ነበር ቦታ ልንቀይር ስንነሳ በጠላት ጥይት ተመታሁ። በዚያው አደርኩ። ዝናብ አደረብኝ። ጠላት ጠዋት አገኘኝ። ስቃይ አድርሶብኛል። ነገር ግን ሙት ያላለኝ ነበርኩና አልሞትኩም” ደምቶ ዝናብ አድሮበት ብርዱ በርትቶበት፣ ህይወቱ አላለፈችም። እየጎተቱ ወደ አለቃቸው ወሰዱት። አንደኛው ይገደል። ሌላኛው ደግሞ ይሰቃይ ይላል። ይሰቃይ የሚለው ሀሳብ አሸንፎ ስቃዩ እንዲበዛበት አደረጉ። ወደ አሁን ተገኝ እየጎተቱ ወሰዱት። ወደ እስታይሽም አመጡት። ስቃዩን ጨርሶ እንደሚሞት አምነዋልና ትተውት ሄዱ። በጥበቡ ጉቼ አማካኝነት የተነሳው ግርማ ከእማሆይ አበበች ጋር ተገናኘ። “እማሆይ ወደ ቤታቸው ወስደው ወተት አጠጡት። ሕዝቡም የሚጠጣ እያመጣ ይሰጠኛል። ቁስሌን እሙሃይ በጨው ታጥብልኛለች። የተለዬ እንክብካቤ ታደርግልኛለች። ቤተክርስቲያን ሄዳ የቁርስ ሰዓቴ ካለፈ ከሰው ጋር ትጣላለች። ለምንድን ነው ያላበላችሁት። እኔ እኮ እንዲድን ነው የያዝኩት እያለች ትጣላለች። ከእናት በላይ ሆነው አቆዩኝ። እየዳንኩ መጣሁ። “ግርማ የእማሆይ መልካም እናትነት ዘላለማዊ ፍቅር ሰጥቶታል። ይህን የመሰለ ሕዝብ፣ ተንከባክቦ የሚያድን፣ ያለ ክፍያ አገልጋዩ ብሆነው፣ ለክብሩ ብዋደቅ ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም ነው የሚለው።
ጤንነቱ እዬተመለሰ ሄደ። እማሆይ ከፀሎት አይቦዝኑም። ለፈጣሪያቸው ምስጋና ከማቅረብ አይቆጠቡም። ግርማም ሲጨናነቅ አይዞህ ልጄ ምንም አትሆንም እያሉ ያበረቱታል። ተስፋም ይሰጡታል። ሕዝብ ማለት እንደ እስታይሽ ሕዝብ ነው እያለ ግርማ ያደንቃቸዋል። ግርማ እማሆይ እንዳዳኑት እና አሁን ላይ የሕመም ስሜት እንደማይሰማው ነው የሚናገረው። “የውትድርና ዓላማው ሞተህ፣ ቆስለህ፣ ምንም ሆነህ ሀገርን ማዳን ነው። እኔ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እታገልለታለሁ ። ነብሴ እስካለች ድረስ ያለ ጫማ አገለግለዋለሁ። ሕዝብ ቢኖር ነው ያዳነኝ። ደብቆ ያቆየኝ ሕዝብ ነው። ይህን ሕዝብ ማገልገል ግድ ነው። እኔ ብሞት እንኳን ልጆቼ ሀገራቸውን እንዲወዱ፣ እንዲያገለግሏት አደራ እሰጣቸዋለሁ። ነብሴ እስካለች ድረስ ሀገሬን ከማገልገል አላቆምም” ነው ያለው።
ግርማ ስለ እማሆይ አበበች ተናግሮ አይጠግብም። መልካም እናት ናቸውና ያነሳቸዋል። ይወዳቸዋል። ያሞግሳቸዋል። “ሕመሙ ሲያበሳጨኝ አንድም ቀን አይቀየሙኝም። አይዞህ የኔ ልጅ ይሉኛል። በእኔ ቤት ሳይሆን በእግዚአብሔር ቤት ነው ያለኸው ይሉኛል። እርሱ ለእናት ሀገሩ፣ ለእኛ ሲል ደሙን ሲያፈስ፣ እኔ ይሄን ባደርግ ምን እጎዳለሁ ይላሉ። ከክብር የበለጠ ክብር ነው የሰጡኝ” ይላቸዋል። እናቴ ነው የሚላቸው። ግርማ ጤንነቱ ሲመለስ ልሂድ፣ ከጓደኞቼ ጋር ተቀላቅዬ ልዋጋ እያለ ያስቸግራቸዋል። እሳቸው ግን መንገድ ላይ ይገድሉሃል እያሉ እንዳሄድ አልፈቀዱለትም ነበር፡፡ ዳሩ ላል ይበላ ነፃ ሲሆን ግርማ ከእማሆይ ተሰናብቶ ሄደ። በመንገድ ላይ እያለ ጠላት አካባቢውን ያዘው። አሁንም ሌላ መውጫ ይፈልግ ነበር። አንድ ደገኛ ሰው አገኙት። እሳቸውም በቤታቸው አስጠለሉት። ቀን እስኪወጣ ድረስ ከእኔ ቆይ እንዲያም ካለ እማሆይ ጋር አደርስሃለሁ አሉት። ግርማ ተስማማ። አንድ ሳምንትም አቆዩት። በአካባቢው ጠላት ሲበዛ እንዳይሞት ስለሰጉ መንገድ አሳይተው ሸኙት። እሱም ጉዞውን ቀጠለ። ሌሎችም መንገድ እያሳዩ የአማራ ልዩ ኀይል ወደ አለበት ሥፍራ አደረሱት። ከእነርሱም ጋር ተገናኘ። ግሩም ነው። የግርማ ቤተሰቦች እማሆይን በአሻገር እየናፈቁ መሆናቸውንም ነግሮናል።

ግርማ በምድር ሁለት እናቶች ተሰጥቶታል። ታድሏልም። ግርማ ምንም እንኳ የሚታገለው ለሀገር ቢሆንም የእርሱ መውደቅ ብዙዎችን ያሳዝን ነበር። አራት ልጆች አሉትና። በናፍቆት የሚጠብቁት፣ እጁን የሚመለከቱት፣ አባታችን እያሉ የሚመኩበት ልጆች ሀዘናቸው ይበዛ ነበር። የልጆቹ እናትም ያለ አባወራ በሀዘን ይቀሩ ነበር። የእነዚያ ልጆች አምላክ ግን ግርማን አተረፈው።
እማሆይም ስለዚያ ቀን ይነግሩን ጀመር። “ቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀምጠን የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ የተጎዳ ሰው እንዳለና እንድንጠይቀው ለአማኙ ተናገሩ። በቤተክርስቲያኑ የነበረው አማኝ ሰማ። እኔም ወተት አፍልቼ ልጠይቀው ሄድኩኝ። ወተቱን ሰጥቼው መጣሁ። በማግስቱ አጥሚት ይዤ ሄድኩኝ። በዚህ መልኩ ይህ ሰው አይድንም፣ ልወሰደው አልኩ። ወሰድኩት። ይህ ልጅ ይድን ይሆን ወይ? ቢሞትብኝስ ምንድን ነው የምሆነው? እያልኩ አስብ ነበር። የመነኩሴ ሥርዓቱ የታመመን መጠየቅ፣ የተቸገረን መርዳት ነውና ይዤው መጣሁ። እግዚአብሔርም አላሰፈረኝም ዳነ። ፈጣሪ ነው ያዳነው ሰው አላደነውም። እርሱ ደሙን ያፈሰሰው ለሀገሩ ነው። ሊነግድ ወይም ሌላ ሥራ ሲሠራ አይደለም ደሙን ያፈሰሰው” ነው ያሉን። እሳቸው ዘመናቸውን በሙሉ መልካሙን ነገር ሁሉ ለማድረግ ይሄዳሉ። መልካሙንም ያደርጋሉ። የእኔን ዋጋ የማገኘው በሰማይ ነው ይላሉ። በምድር ሙገሳ፣ ምስጋና አይፈልጉም። በምድር የሚሠሩትን መልካም ነገር ዋጋውን የሚጠብቁት በሰማይ ነው። ለዚያም ሳይሰለቹ በሠርክ መልካምን ያደርጋሉ። መልካሙንም ይጠብቃሉ። “ያዳነው እግዚአብሔር ነው። እኔ ያደረኩለት ነገር የለም። የእኔ ስጦታ የለም። ምን አልባት ፀሎቴ ነው። ቁጭ ብዬ አድራለሁ። አሁንም ሳልተኛ ፀሎት አደርሳለሁ። ልጆቼ ልጁን ፈጣሪ ፈልጎታል። ወደፊት የሚያደርገው ይኖራል” ነው የሚሉት እማሆይ።
መልካም ነገር አደረኩ ብለው ማውጋት ብዙ አይወዱም። ያደረጉትን ሁሉ ለፈጣሪያቸው ይሰጣሉ። ጠላቶች መጥተው እንዳያዩብኝ ፈጣሪዬ ሆይ ከልለኝ፣ ይህን የእግዚአብሔር እንግዳ ለቤተሰቦቹ አብቃልኝ እያልኩ እማፀን ነበር። ቤቴንም አላዩብኝም፣ ስጋቴ እንዳያዩብኝ እና እንዳይገሉብኝ ነው ያሉን እማሆይ። “እኔ ድኖ ቢዋጋ በጣም ነው ደስ የሚለኝ። ልጆቼን አልሰድም ለሚሉት እጣላለሁ። ታዲያ ለሀገራችሁ ማን ይዋጋ እላለሁ። ግርማም ከዳነ ልጆችህን አይተህ ወደ ነበርክበት ተመለስ ነው ያልኩት እንጂ። ተወውና ውጣ አላልኩትም። አልልም። ሀገር ሀገር ናት” እማሆይ ለሀገር የሚከፈለው መስዋዕት እንዲከፈል ፈቃዳቸው ነው። ሀገር የሁሉም ነገር መሠረት ናትና። ለሀገር ሁሉም ነገር መሰጠት አለበት ብለውም ያምናሉ። ወጣቱ ሀገርን ያስከብር፣ እናት አባትም አይከለክልም ነው የሚሉት።
እማሆይ አርቆ አሳቢ ናቸው። የዓመት ጉርሳቸውን አስቀድመው አዘጋጅተው ነው የሚያስቀምጡት። ይሄም አርቆ አሳቢነታቸው ክፉውን ቀን እንዲያልፉ አደረጋቸው። እማሆይ እሳቸውም እንዲለቁ ግርማንም ይዘው እንዲወጡ በተደጋጋሚ ተጠይቀው ነበር። የእሳቸው መልስ ግን ሬሳዬ ከቤቴ ይወጣል እንጂ አይደረግም ነው። ግርማንም የትም አልከውም፣ ቢድንም ቢሞትም ከቤቴ ነው ነበር መልሳቸው። እንዳሉት አደረጉት። እማሆይ ከግርማ በተጨማሪ ሌላ ሠው ባገኝ ደስ ይለኝ ነበር ነው ያሉን። “እኔ አንድ ባሕሪ አለኝ። ሁሉም የሚለኝ እውነት ነው የሚመስለኝ። እኔም የምናገረው እውነት ነው። እኔ አካሌን ቆርጬ ብሰጥም ምንም አይመስለኝም” በእሳቸው ስስት የሚባል ነገር አይታወቅም። የእጃቸው እስኪያልቅ ድረስ መስጠት ነው። ለእውነት ይኖራሉ። ስለ እውነት ይሠራሉ፣ እውነት ይናገራሉ፣ እውነት ይመሰክራሉ። ውሸትና ውሸታምን አይወዱም። ኢትዮጵያን የሚያድናት እና የሚጠብቃት ኀይል ፀሎት ነው። ሁሉም በፀሎት ይትጋ። የእማሆይ መልእክት ነው።
የእማሆይ ደግነት ግርማን በማስታመም፣ በመንከባከብ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ድንገት ድምፁ የጠፋባቸው ልጆቹና ባለቤቱ እንዳይጨነቁ፣ ሀዘናቸው እንዳይበዛ፣ ተስፋቸው እንደ አለቀ ሻማ እንዳይሆን ዘዴ ፈለጉ። እማሆይ በበቅሎ የአራት ሰዓታት መንገድ ተጉዘው፣ ኔትወርክ ያለበት ቦታ ፈልገው፣ ግርማ ቆስሎ እንደነበር፣ ነገር ግን ደህና እንደሆነ ለልጆቹና ለቤተሰቦቹ ነገሩ። ቤተሰቦቹም ተረጋጉ። በመካከል ስልክ ጠፋና ሳይገናኙ ቆዩ። ሕመሙ አገርሽቶበት ሞቷል ብለው ተጨነቁ። አዘኑ። ግርማ ግን ደህና ነው። እርሱ ድኖ መራመድ ሲችል እማሆይ በደከመ ጉልበታቸው የሁለት ሰዓት መንገድ ተጉዘው ልጆቹና ቤተሰቦቹ እንዲያገኙት አደረጉት። ሞቷል ብለው ተስፋቸው የመነመነው ልጆቹና ባለቤቱ ድጋሜ ተስፋ ሰነቁ። እማሆይ በፀሎት ቤታቸው ተቀምጠው ፈጣሪያቸውን ከማመስገን አይቦዝኑም። በቤተ ክርስቲያን አፀድ ውስጥም አይጠፉም። ጠዋትና ማታ በደብር ናቸው። በተረፈው ሰዓት በቤታቸው ውስጥ ባለች የፀሎት ቤት ያሳልፋሉ። ለሀገርና ለወገን ይፀልያሉ። እርሳቸውን የሚመስል ማን አለ? የትስ ይገኛል? ያ ክፉ ቀን አለፈ።
በስቃይ ይሞታል የተባለው ግርማም ዳነ። እናት እንዲህ ናት። የተራበን የምታጎርስ፣ የታረዘን የምታለብስ፣ ያዘነን የምትዳብስ፣ በፍቅሯ የምትፈውስ። ግርማ በእማሆይ እጅ ተዳብሶ፣ በእማሆይ እጅ ጎርሶ፣ በእማሆይ ፍቅር ተፈውሶ ያን ቀን አልፏል። ፍቅራቸው አስቀናኝ፣ የእናትነት ጥጋቸው አስገረመኝ። የደግነት ወሰናቸው ደነቀኝ። ምን ይባላል በምድሯ ይኑሩ። ዘመንዎ ይባረክ እድሜ ይስጥዎት ከማለት ውጭ። ምን አይነት መሰጠት፣ ምን አይነት ደግነት ፣ ምን አይነት መልካምነት ይሆን። በእናትነት ፍቅራቸው እየቀናሁ። ዳግም ያገናኘን ዘንድ ተመኝቼ፣ ተመርቄ ተሰናበትኳቸው። አካሌ ከቤታቸው ወጣ እንጂ መንፈሴ ግን ከእርሳቸው ግርጌ ተጠልሎ ሲመረቅ ይኖራል።
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ!!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleThe TPLF turned schools into burial sites in Amhara Region, Ethiopia.
Next article❝ዲያስፖራው ወደ ሀገር መግባት ከወገኑ ጎን እንዲቆም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለውን ያልተገባ ጫና ለመቀልበስና የበቃ ንቅናቄን ለማፋፋም ያግዛል❞ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ