
ታኅሣሥ 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) መሰሪነቱን እና ሀገር አፍራሽነቱን ቀድማ ተረድታ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድንን ከሥልጣን ዘመኑ ጀምሮ አጥብቃ ታግላዋለች፡፡ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥልጣን የመጣበትን የሸፍጥ መንገድ እና ለሥልጣን ሲል የገደላቸውን፣ ያሰራቸውን እና እንዲሰደዱ ያደረጋቸውን የሀገር ባለውለታዎችን ማንነት እና ታሪክ ከታላላቆቿ ስትሰማ ነው ያደገችው፡፡ ባደገችበት አካባቢም በርካታ ጀግኖች ይህንን ሀገር አፍራሽ አሸባሪ የትግራይ ወራሪ ቡድንን ጨምሮ የውጭ ጠላቶች ጋር ተጋድሎ ያደረጉበት በመሆኑ የትኛው ተራራ ምን ጀብድ ተፈጽሞበታል የሚለውን ስትተርክ እጅን በአፍ ታስጭናለች፡፡
ስለ ሀገሯ ታላቅነት እና ስለ ማንነቷ ቀድሞ ነው የገባት፤ ፋኖ ዘነቡ መንግሥቴ፡፡
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን የሥልጣን መንበሩን እንደተቆናጠጠ ከደደቢት በረሃ ጀምሮ በጠላትነት የፈረጀውን የአማራን ሕዝብ ለም መሬቱን እየነጠቀ፤ ሃብቱን እየቀማ ገድሎታል፤ አፈናቅሎታል፤ እንዲሰደድ አድርጎታል፡፡
ማንነቴን፣ ርስቴን እና ቀዬን አለቅም ያለውንም በማንነቱ ተሸማቆ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ ይህ የግፍ ግፍ የገባት ፋኖ ዘነቡ መንግሥቴ በአማራ ላይ የሚደርስ ግፍ ሊቆም ይገባል ስትል ትግል የጀመረችው ገና በጠዋቱ ነበር፡፡ በዚህም የጠለምት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ውስጥ በንቃት በመሳተፍ ለአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የእግር እሳት ሆነችው፡፡ ይህ ሀገር አፍራሽ ቡድን ከአማራ ጫንቃ ብሎም ከኢትዮጵያ ምድር ካልተነቀለ ትዳር እና ቤተሰብ ላትመሰርት ለራሷ ቃል ገብታ ትግሏን ቀጠለች፡፡
ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊ ዕሴት ደንታ የሌለው አሸባሪው የትግራይ ቡድን የዋልድባ ገዳም እና መነኮሳት ላይ ይፈጽም የነበረውን በደል እና ግፍ በመቃወም ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ሌላ ትግል ጀመረች፡፡
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድንም ሴራውን እያጋለጠች ያስቸገረችውን ይህችን ትንታግ ወጣት በተለያየ የፈጠራ ክስ በተደጋጋሚ ለእስር ዳርጓታል፤ ሀገር ለቃ እንድትሰደድ ጫና ተደርጎባታል፤ እሷ ግን ወይ ፍንክች፡፡ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከሥልጣን ተወግዶ መቀሌ እንዲደበቅ በተደረጉ ሕዝባዊ ተጋድሎዎች በንቃት ተሳትፋለች፡፡ አሸባሪው ቡድን ከስልጣን ተወግዶ ሕዝቡ ነጻ መውጣቱ ደስታዋን ወደር አሳጣው፡፡ ስለቷ ሰምሮ የትዳር አጋር ያዘች፤ አሁን እንደ ሌሎች እህቶቿ መኖር ጀመረች፡፡

“ያደቆነ ሰይጣን…” እንዲሉ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን መቀሌም አርፎ በሰላም መቀመጥ አልወደደም፡፡ የባንዳነት ማንነቱ አለቀው ብሎ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ከጀርባው ወጋ፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ታውጆ በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ፍም ክንዶች ተለብልቦ በሁለት ሳምንታት ብቻ አፈር እንዲገባ ተደረገ፡፡ በዚህም አላበቃም የተበታተነ ኀይሉን ሰብስቦ “ሀገር አፈርሳለሁ፤ ከአማራ ሕዝብ የማወራርደው ሒሳብ አለኝ” ብሎ ወረራ ፈጸመ፡፡ ፋኖ ዘነቡ ነፍጥ አንስታ በአማራ ፋኖ ውስጥ ትግል ገባች፡፡ ባለቤቷም በሌላ ግንባር ፍልሚያውን ተቀላቀለ፡፡
ፋኖ ዘነቡም ከጓዶቿ ከነ ፋኖ አጋዬ አድማስ ጋር በመሆን አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን በገባበት ገብተው እየቀበሩት ነው፡፡ ነገሮች በሥልጣን ዘመኑ እንደነበረው ቀላል መስሎት ውጊያ የገጠመው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን እነ ፋኖ ዘነቡ እና የፀጥታ ኀይሉ ፊት ከቶ መቆም እንዴት ይቻለው፤ የተቀበረው ተቀብሮ፣ የተማረከው ተማርኮ የተቀረው መግቢያ ጠፍቶት እየተቅበዘበዘ ነው፡፡
ፋኖ ዘነቡ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ ዘግናኝ እና ይቅር የማይባል ስትል ነው የምትገልጸው፡፡ ሴት፣ ወንድ፣ ሕጻን፣ አዋቂ ሳይል ሲገድል፣ ሲያስር እና ሲያፈናቅል የነበረው አልበቃ ብሎት ዳግም ወረራ በመፈጸም ሌላ ግፍ መጨመሩ የሽብር ቡድኑን የሀገር ነቀርሳነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ባይ ናት፡፡ እናም ይህንን ባንዳ የሽብር ቡድን ከስሩ ለመንቀል ከጓዶቿ ጋር እየተፋለሙት እንደሆነ ተናግራለች፡፡
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ብቻ በሴቶች ላይ የፈጸመው ግፍ እና በደል የትኛዋም ሴት ምንም አልሆንም ብላ እንዳትቀመጥ ማሳያ በመሆኑ በተለይ ወጣቶች ከፀጥታ ኀይሉ ጋር በመሰለፍ ይህንን የሀገር ነቀርሳ ከነ አስተሳሰቡ መንቀል ይገባቸዋል ብላለች፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ በየአውደ ውጊያው እየፈጸሙት ያለው ጀብድ ኢትዮጵያ የምንግዜም ጀግኖች ሀገር መሆኗን አረጋግጧል፡፡ አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን አስከመጨረሻው #ለመቅበር ፋኖ ዘነቡን ጨምሮ በርካታ አናብስት ከወንድሞቻቸው ጋር በግንባር ይገኛሉ፡፡
በተለይ ወጣቶች ቤት ውስጥ ሆኖ የጠላትን የግፍ ቀንበር ከመቀበል እና የሕይወት ዘመን ጠባሳ እንዲደርስባቸው ከመፍቀድ ይልቅ ዘመቻውን ተቀላቅለው ጠላትን ድል ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው የሚለው የፋኖ ዘነቡ መልዕክት ነው፡፡
ዘጋቢ፡-የማነብርሃን ጌታቸው
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
