አሸባሪው ትህነግ በቆቦ ከተማ በአንድ ቀን 89 ንጹሃንን ገድሎ በጅምላ መቅበሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

257

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በቆቦ ከተማ ንጹሐንን በጅምላ ጨፍጭፏል። የሟች ቤተሰቦችም አስከሬን እንዳያነሱና እርማቸውን እንዳያወጡ በመከልከል ይቅር የማይባል ግፍ መፈጸሙን ገልጸዋል።
የከተማው ነዋሪ አቶ አበበ ዘውዴ እንደገለጹት በከተማው በሦስት ዙር ከተደረገው ውጊያ የበለጠ የሚከፋው የራያ አርበኞች፣ ሚሊሻና ታጣቂዎች የሽብር ቡድኑን ለመከላከል ጳጉሜን 04/2013 ዓ.ም ያደረጉት ነው።
አሸባሪው ትህነግ ቡድንም በዚህ ቂም በመያዝ በየአካባቢው አርሶ አደሮችንና እናቶችን መጨፍጨፉን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት 600 የሚደርሱ ንጹሃንን በመጨፍጨፍ መቀበራቸውንም ተናግረዋል።
በቆቦ ከተማ ብቻ ጳጉሜን 05/2013 ዓ.ም አሸባሪው ትህነግ የጨፈጨፋቸው 89 ንጹሃን ዜጎች በጅምላ መቀበራቸውን አመልክተዋል።
በማግስቱም 16 ንጹሃን ተቀብረዋል። ይህ አሐዝ በአካባቢው ገጠር ቀበሌዎች የተቀበሩትንና የተሰወሩትን እንደማያካትትም አቶ አበበ ጠቁመዋል።
ሦስት የቤተሰባቸው አባል የተገደሉባቸው ወይዘሮ ወርቄ ጉብሳ፤ በዕለቱ በአካባቢያቸው ከፍተኛ የተኩስ እሩምታ ይሰማ ነበር ብለዋል።
ምሽት 11:00 ሰዓት ገደማ ቤት ውስጥ በመግባት ሰባት ሆነው ተሸሽገው ከነበሩት ህጻናትን ትተው አራቱን እንደወሰዷቸው ተናግረዋል።
‹‹እባካችሁ አትውሰዷቸው፣ ገበሬ ናቸው የሚያውቁት ነገር የለም ብላቸውም ተጠይቀው ይመለሳሉ በማለት እየገፈተሩና እየተቆጡ እንደወሰዷቸው፣ አንደኛውን ክንዱን መትተውት ቆስሎ መመለሱን›› አስታውሰዋል።
“በነጋታው ማለዳ ተነስቼ ፍለጋ ወጣሁ ከእኔ ቤተሰቦች ጭምር አራት ሰዎች አንድ ቦታ ተገድለው አገኘኋቸው፤ ነጠላ አለበስኳቸው፤ ተደፍቼ አለቀስኩ” ብለዋል።
“አንቺንም እንዳንገድልሽ ዝም በይ” በማለት እንዳስፈራራቸው ጠቁመዋል።
“እኔንም ግደለኝ” ቢሉም በማመናጨቅና በመገፈታተር እንዳባረራቸው ይናገራሉ።
አስከሬኖቹ ጸሃይ ላይ ውለው አድረው ሽማግሌ ተልኮ ሳያለቅሱ እንዲያነሱ እንደተፈቀደ ተናግረዋል።
ሁለት ወንድሞቻቸውና የእህታቸው ባለቤት የተገደሉባቸው ወይዘሮ ጉዝጉዝ እጅጉ እንደገለጹትም፤ አስከሬን ከወደቀበት ያነሱት ሽማግሌ ልከው መሆኑን፣ በኬሻ ጠቅልለው አስክሬኖቹን ሳያጥቡ መቅበራቸውን ገልጸዋል።
በዕለቱ ጉድጓድ የሚምስ ጠፍቶ ብዙዎችን እየደራረቡ ሲቀበሩ መመልከታቸውን፣ እንዳያለቅሱ መከልከላቸውን በመጠቆምም፤ ምሽት ቤት እያንኳኩ ሲያስቸግሯቸውም ጥለው ወደ ገጠር መሰደዳቸውን ተናግረዋል። ሲመለሱም ቤታቸው ተዘርፎና ወድሞ እንዳገኙት አመልክተዋል።
የተጎጂዎቹ ጎረቤት አቶ ሞላ ንጉሴ አራት ልጆች አንድ ቦታ መገደላቸውን እንደተመለከቱ ተናግዋል። የዘገበው ኢፕድ ነው።
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleለአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ተባባሪ የነበሩትን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ቢሮው ገለጸ፡፡
Next article“የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከአሸባሪው ትህነግ ዘረፋ በተረፈው ንብረት እንኳን መስራት እንዳይችል ሆኖ ወድሟል” የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው