
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ለአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በመተባበር በሕዝቡ ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ገረመው ገብረጻዲቅ በአማራ ክልል ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ማሻሻያ የተደረገባቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ ለአሚኮ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው ስድስተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሰባተኛ አስቸኳይ ስብሰባ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር ውይይት በማድረግ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፤ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል ነው ያሉት አቶ ገረመው፡፡
በመግለጫቸው እንዳሉት ምክር ቤቱ የክልሉን የሕልውና ዘመቻ ለማስፈጸም በመመሪያ ቁጥር 46/2014 ካስቀመጣቸው ክልከላዎች መካከል በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ክልከላ በተወሰነ መልኩ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡
የጸጥታ ኀይሎች ጥምረት በአሸባሪው የትግራይ ወራሪው ቡድን ላይ በወሰዱት ርምጃ ድል መገኘቱን ተከትሎ ከምሽት 2፡00 እስከ ንጋት 12፡00 ሰዓት የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ከምሽት 4፡00 እስከ ንጋት 11፡00 እንዲሆን ተወስኗል ብለዋል፡፡ ጦርነቱ ቀጣይነት ቢኖረውም የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል አስፈላጊ በመሆኑና ከተሞችን በማነቃቃት በሂደት ሕዝቡን ወደ መደበኛ እቅስቃሴ ለማስገባት የተላለፈ ውሳኔ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡
ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ነጻ በወጡ አካባቢዎች በየደረጃው ያለ ኮማንድ ፖስት የጸጥታ ሁኔታውን እየገመገመ ማሻሻያ የሚያደርግ ሲሆን እስከዚያው የበፊቱ መመሪያ ተፈጻሚ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል የሥራ ማስኬጃ በጀታቸውን ለኅልውና ዘመቻው ሲያውሉ የነበሩ የክልሉ የመንግሥት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲመለሱ እና ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ውሳኔ መተላለፉን ገልጸዋል፡፡
ለኅልውና ዘመቻው አስፈላጊ ከሆኑ ባለሙያዎች እና የሥራ ኃላፊዎች በስተቀር ሁሉም ባለሙያዎች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲገቡ ተወስኗል፡፡ ተቋማት ያልተፈጸመውን የበጀት ዓመቱን ዕቅድ መልሶ በመከለስ በቀሪ ወራት ማካካስ ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ግንባር በመሰለፍ ያሳዩትን ቁርጠኛ ተጋድሎ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ሥራቸውን በመፈጸም ሊደግሙት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሕግ ማስከበርን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ከሕግ አግባብ ውጭ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን የጸጥታ ተቋማትና ኅብረተሰቡ ተባብረው ማስቆም ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ እንደተጠበቀ ሆኖ ማስተማር ቅድሚያ ይሰጠዋል ብለዋል፡፡ መንግሥት ሕገወጥነትን አይታገስም ብለዋል።
በሌላ በኩል ለአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን መረጃ በመስጠት፣ ቦታዎችን በማሳዬት እና በልዩ ልዩ መንገድ ተባባሪ ሆነው በሕዝቡ ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ ጉዳያቸው በመደበኛው የሕግ ሥርዓት የሚሸፈን ሆነው የተገኙትን እልባት የመስጠት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም ራሱን የቻለ የመርማሪዎች ቡድን መደራጀቱን ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ በዐቃቤ ሕግ የሚመራ ሲሆን ልዩ ልዩ ተግባራትን አከናውኗል ነው ያሉት፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሸፈን ከሆነ ግን ራሱን የቻለ የሕግ ሥርዓት አለው ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ጥቆማ በመስጠት የሚተባበረውን ያሕል ማስረጃ በመሆንና ምስክርነት በመስጠት እንዲያግዝም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
