
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት የተለዬ ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆቹን የሚያስተምርበት አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲከፈትለት ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ከመንግስት መልስ በማጣቱ ሕዝቡ ቁጭት ውስጥ ቆይቷል፡፡ የአማራ ክልል ሕዝቦች በራስ አቅም መልማትን ሰንቆ ኅብረተሰቡን እያስተባበረ በሚሠራው የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አስተባባሪነት ኢንጅነር ፀደቀ ይሁኔ በተባሉ ባለሃብት አማካኝነት ከ29 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ገንዘብ የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተገንብቶ በ2011 ዓ.ም ትምህርት ጀምሮ ነበር፡፡
የነገ ሀገር መሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የቴክኖሎጅ አፍላቂ ምሁራንን ለማፍራት ታስቦ ትምህርት ቤቱ ሲከፈት በበርካቶች ዘንድ ትልቅ ተስፋ ፈንጥቋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት ይህ ትምህርት ቤት የሚተዳደርበት የራሱ ዝክረ ሕግ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ እንዲገባ የራሱን ሚና ተወጥቷል፡፡ ለዚህ ትምህርት ቤት የወሎ ዩኒቨርሲቲ በየዘርፉ ስመ ጥር የሆኑና የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸውን መምህራን በልዩ ሁኔታ በመመደብ የኮምፒውተር፣ የፊዚክስ፣ የሥነ ህይወትና የኬሚስትሪ ቤተ ሙከራዎችን እንዲደራጁ አድርጓል፡፡
የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የተማሪዎችን ፍራሽ፣ አንሶላና ብርድ ልብስ አሟልቷል፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለአዳሪ ትምህርት ቤቱ የተሻለ ብቃትና ችሎታ ያላቸውን መምህራን በመመደብ ወደ ሥራ ገብቶ ነበር፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት ከአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች የተመረጡ 285 ባለልዩ ተሰጥኦ ተማሪዎች በመማር ላይ ነበሩ፡፡ ትምህርት ቤቱ በ2014 የትምህርት ዘመን ጥቅምት 25 ትምህርት ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቅቆ ተማሪዎቹን ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ ነበር፡፡
ነገር ግን አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ደሴን ተቆጣጥሮ በቆየበት ወቅት ትምህርት ቤቱን እንዳልነበር አድርጎት ሸሽቷል፡፡
ገንዘብና ጉልበት የፈሰሰባቸውን የኮምፒውተርና የሳይንስ ቤተ ሙከራዎችን የቻለውን ዘርፎ ያልቻለውን አውድሟል፡፡ የተማሪዎች ማደሪያ ዶርም ውስጥ የነበሩ አልጋ፣ ብርድ ልብስ፣ ፍራሽ ዘርፏል፡፡
የተማሪዎች መታከሚያ ክሊኒክ ውስጥ የነበሩ መድኃኒትና የቤተ ሙከራዎችን እቃዎችን ወስዷል፡፡
ለተማሪዎች ቀለብ የተዘጋጀ ጤፍ፣ ሽሮና በርበሬ ዘርፏል፡፡ የተማሪዎችን መመገቢያ ማንኪያ እንኳን ሳያስቀር ወስዷል፡፡
በትምህርት ቤቱ በአጠቃላይ ከ23 ሚሊዬን ብር በላይ የሚያወጡ ንብረቶች በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ዝርፊያን ወድመት መደረሱን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ በለጠ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ቤቱን መውደምና መዘረፍ የሰሙ ተማሪዎችና መምህራን ማዘናቸውን የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር ዓለምነው አበራ ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ቡድን በቅናትና በምቀኝነት ትምህርት ቤቱን እንዳልነበር አድርጎታል፡፡ በተማሪዎችና መምህራን ዘንድ ቁጭትን ፈጥሯል፡፡
ይሁንና የነገ ተስፋ የሰነቅንባቸው እንቁ ተማሪዎች የሚማሩበት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ወደ ቀድሞ የመማር ማስተማር ሥራው እንዲመለስ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ትምህርት ቢሮ ጠይቋል፡፡
መረጃው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ነው
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
