“በአማራ ክልል ሕገወጥ ተኩስ በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ

293

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ ሰላም አቸነፍ ሰሞኑን ከዘመቻ መልስ በነበረው ተኩስ እሳቸውን ጨምሮ ልጃቸው እንቅልፍ አጥተው እንደነበረ አስታውሰዋል። ድርጊቱ ሰላምን የሚያውክና የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሽ ስለኾነ መንግሥት በአፋጣኝ ሕግን ሊያስከብር እንደሚገባ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በጸጥታ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
የወገን ጦር አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድንን በመደምሰስ አኩሪ ድል እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል። በተደረገው አኩሪ ተጋድሎ በርካታ አካባቢዎች ከሽብር ቡድኑ ነጻ ወጥተዋል ነው ያሉት።
ከዘመቻ የሚመለሱ የጸጥታ ኃይሎች ወደየአካባቢያቸው ሲያቀኑ ጥይት ያለአግባብ መተኮስ ተገቢ አይደለም ብለዋል። ከግንባር የተመለሰ የጸጥታ ኃይል እንዴት ሰላማዊ ሕዝብ ውስጥ ገብቶ ይተኩሳል? በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል።
ሕዝብ ውስጥ እየተኮሱ ሰላምን የሚያውኩ ሰዎች የፈጸሙት ድርጊት ወንጀል ስለኾነ ማንኛውን ድርጊቱን የፈጸመ አካል በሕግ ይጠየቃል ነው ያሉት። ድርጊቱ አሳፋሪ መኾኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ዘማቹ አካል ከግንባር ወደ ባሕር ዳር ከተማ በተመለሰበት ወቅት አላስፈላጊ ተኩስ በመፈጸሙ ከስድስት ሰዎች በላይ ቆስለዋል፣ ሕፃናት፣ እናቶች እንዲኹም ኹሉም ሰላማዊ ነዋሪዎች መረበሻቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ድርጊቱ የሀብት ብክነት ብቻ ሳይኾን የአካባቢውን ሕዝብ ሰላም የሚያውክ፣ በወታደራዊ ሥነምግባር የሚከለከል እንደኾነም ኮሚሽነር ተኮላ አስገንዝበዋል።
“ድርጊቱ ከተሰለፍንበት ዓላማ ተፃራሪ ኾኖ ነው የተገኘው” ብለዋል። በክልሉ ማንኛውም አካል ያለቦታው የሚተኩስ ከሆነ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
“ከተሞቻችን የቱሪስት ማእከል ስለኾኑ በአላስፈላጊ ተኩስ ሰላም ማጣት የለባቸውም” ብለዋል።
የጸጥታ አካሉ ችግሩን ለመቅረፍ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ኅብረተሰቡ ተባባሪ መኾን እንዳለበት ኮሚሽነር ተኮላ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleበሀገራዊ ጥሪው ወደ ሀገር የሚገቡ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
Next articleየይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በአሸባሪው ቡድን ከ23 ሚሊዬን ብር በላይ የሆነ ንብረት ዝርፊያና ውድመት እንደደረሰበት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡