
የብሮድካስት ባለሥልጣን ጥፋት እና ግጭት ቀስቃሽ መገናኛ ብዙኃን ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ።
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ሥራዎች፣ ውስንነቶች እና መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በባሕር ዳር ተካሂዷል። ምክክሩ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ነባራዊ ሁኔታ እና ለውይይቱ በቀረበው ጽሑፍ ላይ ትኩረት አድርጎ ነው የተካሄደው።
በመወያያ ጽሑፉ እንደቀረበው ሙያውን በማያውቁ ሰዎች ሚዲያን መምራት፣ በመገናኛ ብዙኃን የሥሜት እና የዕውነት መቀላቀል፣ በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡ ሰዎች ከዕውነት እና ከዕውቀት ይልቅ ምን ይሉኛልን በማሰብ መናገራቸው፣ የሙያዊ አቅም ማነስ እና ሌሎችም በውስንነት ቀርበዋል።
በነባራዊ ሁኔታው ደግሞ ብሔርን እና የፓርቲ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ መገናኛ ብዙኃን መበራከት ከስነ ምግባር ጉድለት ጋር ተዳምረው ችግሩን እንዳባባሱት ተጠቅሷል።
ሙያዊ አቅምን በተከታታይ ሥልጠና ማጎልበት፣ ከሙያው ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ሰዎች ወደ ሙያው አለማስገባት፣ ሙያን ከሥነ ምግባሩ አኳያ ማከናወን፣ የብሮድካስት ባለሥልጣን ደግሞ ህግን የሚተላለፉ መገናኛ ብዙኃን ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት የሚሉ ሀሳቦች በመፍትሔነት ቀርበዋል። በሚዲያ ባለቤትነት ላይም ማስተካከያ ማድረግ እንደሚገባ ነው የተጠየቀው።
ግጭት ቀስቃሽ እና የተዛቡ ታሪኮች የሚያቀርቡ፣ በግልፅ ብሔር ተኮር ጥቃት እና የሥም ማጥፋት የሚፈጽሙ፣ የአንድን ወገን ሀሳብ የሚያቀርቡ እና ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚያሰፉ መገናኛ ብዙኃን በተጨባጭ እየታዩ መንግስት ዝምታን ለምን መረጠ? የሚሉ ጥያቄዎች ከተወያዮቹ ቀርበዋል።
የግለሰቦችን ሰብዕና መገንባት ላይ የተጠመዱ፣ ሕዝብ እና ብሔር የሚሰደብባቸው መገናኛ ብዙኃንም በዝምታ መታለፍ የለባቸውም፤ በምሁራን ሽፋን የትውልድን አዕምሮ የሚያውኩ መረጃዎችን የሚያቀርቡትንም ተጠያቂ ማድረግ ይገባል ሲሉ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶክተር) ብዙዎቹ የተነሱት ችግሮች የሥነ ምግባር እንደሆኑና ችግሮችን በሥልጠናና በምክክር ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ብሮድካስት ባለሥልጣን በህግ የተሰጠውን የሕዝብ አደራ ለመወጣት ህጉን ተከትሎ ማስተካከያ ይወስዳልም ብለዋል። መረጃዎችን በማደራጀት እና በመተንተን አስተውሎት በተሞላበት መልኩ ግብረ መልስ እና ምክር እንደሚሰጥ እና በዚህ በማይስተካከሉት ላይ ግን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል።
መገናኛ ብዙኃን ሁሉም ስሜቱን በሕዝብ ላይ የሚያራግፍባቸው እንዳይሆኑ ባለሥልጣኑ እንደሚሰራም ዶክተር ጌታቸው ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ ዝምታን መርጦ ሳይሆን ስህተቶችን እንዲያርሙ ዕድል በመስጠት የፕረስ ነፃነትን ለማጎልበት እንጂ የትኛውም ሕዝብ ኃላፊነት በጎደላቸው መገናኛ ብዙኃን ጥቃት እንዲደርስበት አንፈልግም፤ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድም እናደርጋለን ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።
በውይይቱ የተሳተፉት የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት መምህራን፣ የመገናኛ ብዙኃን እና የማስታወቂያ ባለሙያዎች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የኅብረተሰብ ተወካዮች ናቸው።
ይህም ተቋሙ አሠራሩን እና ተጠያቂነቱን ለሕዝብ ግልፅ በማድረግ ሕዝቡ ችግሮችን ሲመለከት ጥቆማ እንዲያቀርብ እና ባለሥልጣኑንም ለመጠየቅ እንዲችል ያደርጋል ብለዋል ዶክተር ጌታቸው።
ዘጋቢ፦ አስማማው በቀለ