
ደብረማርቆስ፡ ታኅሣሥ 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምእራባዉያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት በሕዝብ የተመረጠውን መንግሥት በማስወገድ አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን ወደ ስልጣን ለማምጣት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጥረት አድርገዋል፡፡ የዓለም ማኅበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ ያለውን እውነታ እንዳይረዳ የሚዲያ ዘመቻም ከፍተዋል፡፡
ይህን ጫና ለመቀልበስም ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ውሎ አዳራቸውን ምሽግ አድረገው ረሃቡን እና ቁሩን ተቋቁመው ዳገት ቁልቁለቱ ሳይበግራቸው ጠላትን እያሳደዱት ይገኛሉ፡፡ ሌላው ሕዝብም ለጀግኖቹ ደጀን በመሆን ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ የ”በቃ” ዓለም አቀፍ ንቅናቄን በመፍጠር የሽብር ቡድኑን ሴራ እና የምዕራባውያንን የጥፋት መንገድ እርቃኑን ሲያስቀሩ ዓለም የኢትዮጵያዊያንን እውነት እንዲረዳም እንደ አባቶቻቸው በአንድነት መንፈስ ዘመቻውን በመላው ዓለም አዳርሰዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የዚሁ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ አካል በመሆን የምእራባውያንን ጫና ለመመከት ዓላማ ያደረገ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡ በመድረኩም የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ይሄይስ አለሙ (ዶክተር) ኢትዮጵያ የምእራባውያኑን አፍሪካን የመቀራመት የቀኝ ግዛት ሴራ ያከሸፈች እና የጥቁርን አሸናፊነት ያበሰረች ሀገር በመሆኗ በሥጋት ያዩዋታል፤ ለዚህም አጋጣሚውን ባገኙ ጊዜ ሁሉ የኢትዮጵያን ሰላም መሆን እና ማደግ አይሹም ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ እያደረጉት ያለው ጫናም ለዚህ ሴራቸው ማሳያ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡ ዶክተር ይሄይስ የምእራባውያን ጫና ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ምድር የሽብር ቡድኑ አስተሳሰብም መቀበር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
የምእራባዉያን ጫና እና የምሁራን ሚና በሚል የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህር አዳነ ካሴ (ዶክተር) ምእራባውያን ኢትዮጵያ በጣሊያን በተወረረች ወቅት በሊግ ኦፍ ኔሽን የንጉሱን ጥያቄ ውድቅ ከማድረግ ባለፈ ከኢትዮጵያ ላይ የጦር መሳሪያ ማእቀብ በመጣልም ጠላትነታቸውን በግልፅ አሳይተዋል፤ አሁን ያደረጉትም ከዚሁ የተለየ አይደለም ብለዋል፡፡
ዶክተር አዳነ ምሁራን ሃሳብ በማመንጨት የሕዝቡን ችግሮች በመለየትና መፍትሔ በማፈላለግ የመሥራት ኀላፊነት እና አደራ እንዳለባቸውም አስረድተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር መኮነን አለኸኝ (ዶክተር) የአማራ ሕዝብ ጠላት የሆነው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን አማራን ለማጥፋት የመጨረሻውን ሙከራ አድርጓል፤ ይህም እቅድ ለረጅም ዓመታት የታቀደና የተተገበረ ሴራ ነበር ብለዋል፡፡ በመሆኑም የአማራ ሕዝብ አንድነቱን በማጠናከር በክልሉ ውስጥ አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ እና አስተሳሰቡን ዳግም እንዳይነሳ መቅበር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ በቀጣይም የአማራ ሕዝብ እና መንግሥት እጅ እና ጓንት ሆነው መሥራት፤ የሕዝቡን ጥቅም ማስጠበቅ፤ ጠንካራ የፀጥታ ኀይል ማደራጀት፤ ጦርነቱ ያደረሰውን ጉዳት በማሰብ ከመቆዘም ይልቅ ከደረሰው ጥፋት በመማር ለመፍትሔው መትጋት ወሳኝ ጉዳዮች ስለመሆናቸው ተነስቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ዘላለም አስፋው-ከደብረማርቆስ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
