
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት ተወያይቶ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን እና በተወሰኑ ጉዳዮች ዙሪያ ማሻሻያ ማድረጉን የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በከፈተው ወረራ የክልሉ መንግሥት የክተት ጥሪ አስተላልፎ እንደነበር ያወሱት የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኅላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ የክተት ጥሪውን ተቀብለው በግንባር፣ በሎጀስቲክስ፣ በፕሮፖጋንዳ እና በደጀንነት ለተሳተፉት ሁሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡
በክተት ጥሪው የክልሉ መንግሥት ተቋማት መደበኛ ሥራዎቻቸውን አቁመው ወደ ኅልውና ዘመቻው እንዲዞሩ እና በጀታቸውም ለዚሁ ዓላማ እንዲውል አስገዳጅ ውሳኔ ተወስኖ ነበር፡፡
የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት በውይይቱ አሁን የተገኘውን አንፃራዊ ድል ከግምት ውስጥ በማስገባት ተቋማት መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲጀምሩ እና በየደረጃው ከሚገኙ ሠራተኞቻቸው ጋር በመወያየት እቅዳቸውን አሻሽለው እንዲጀምሩ ወስኗል፡፡ የተፈናቀሉ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ፣ የኅልውና ዘመቻውን ለመደገፍ የወጡ የመንግሥት ሠራተኞች ተመልሰው ከመደበኛ ሥራቸው ጎን የኅልውና ዘመቻውን እንዲደግፉም ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ከቀበሌ እስከ ዞን የፈረሱ ተቋማትን አደራጅቶ ወደ ሥራ የማስገባቱ ሥራ እየተጠናቀቀ ነውም ተብሏል፡፡
የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ በሚመለከት የተወያየው የክልሉ ካቢኔ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የ24 ስዓት የተጠናከረ የጥበቃ አገልግሎት እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በኬላዎች፣ መግቢያና መውጫ በሮች እና በተመረጡ አካባቢዎች ፍተሻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ኅላፊው ሕዝቡ በተለይም ወጣቶች የየአካባቢያቸው የሰላም አርበኛ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡
አቶ ግዛቸው እንዳሉት ስርቆት፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ ዘረፋ እና የሕዝቡን ሰላም የሚነሱ ጉዳዮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል። ድልን ምክንያት አድርጎ በየአካባቢው የሚደረግ ተኩስ ተገቢ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ላለፉት ስድስት ወራት ሰላም እና እንቅልፍ አጥቶ ቆይቷል ያሉት አቶ ግዛቸው የሕዝብን ሰላም የሚረብሹ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል፡፡ እንደየ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ የሚተገበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ማሻሻያም ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ሌላው የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት አቅጣጫ ካስቀመጠላቸው ጉዳዮች መካከል በቅርቡ የሚከበሩ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን የሚመለከት ነው፡፡
በጦርነቱ ምክንያት የተጎዳውን የክልሉን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ለመደገፍ በዓላቱ ትልቅ ሚና አላቸው ያሉት አቶ ግዛቸው ጥሪ የተደረገላቸው የዲያስፖራው ማኅበረሰብም ወደ ክልሉ ይመጣሉ ብለዋል፡፡ እንግዶችን ያለምንም የጸጥታ ስጋት አስተናግዶ ለመመለስ ሁሉም የጸጥታው ባለቤት መሆን አለበት ነው ያሉት አቶ ግዛቸው፡፡ ሕዝቡም የልደት በዓልን በላልይበላ እና ጥምቀትን በጎንደር በተረጋጋ ሁኔታ እንዲያከብር ቅድመ ዝግጅቶች ተጀምረዋል ነው ያሉት፡፡
በአጠቃላይ የክልሉ መንግሥት መሥተዳድር በመላው ኢትዮጵያዊያን የጋራ ርብርብ ለተገኘው ድል እውቅና ሰጥቶ ድሉ ዘላቂ የሚሆነው ተጎጂዎች ከጉዳታቸው ሲያገግሙ እና የሽብር ቡድኑ ሲጠፋና አመለካከቱ ለመጨረሻ ጊዜ ሲከስም በመሆኑ ለቀጣይ ግዳጆች የተለመደ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግም አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል አቶ ግዛቸው በመግለጫቸው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
