“ከኅልውና ዘመቻው ዓላማ አንፃር ጦርነቱ አልተቋጨም፤ በዘመቻው አኩሪ ገድል ለፈጸሙ የወገን ጦር አባላት የክልሉ መንግሥት ክብር አለው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

114

ታኅሣሥ14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ትናንት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክሮ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ላለፉት ሰባት ወራት ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶችን አድርሷል፡፡ ከደረሰው ዘርፈ ብዙ ጉዳት መልሶ ለማገገም የክልሉ መንግሥት የድጋፍ ጥሪም አቅርቧል፡፡
የክልሉን ካቢኔ የምክክር አቅጣጫዎች አስመልክተው ለብዙኀን መገናኛ ተቋማት መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ የአማራ ሕዝብ ወደ ኅልውና ዘመቻው ሲገባ ካስቀመጠው ዓላማ አንፃር ጦርነቱ አልተጠናቀቀም ብለዋል፡፡
የኅልውና ዘመቻው ዓላማ ለአማራ ሕዝብ ብሎም ለኢትዮጵያ ኅልውና ስጋት የሆነውን አሸባሪ ቡድን ማክሰም ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ይህ እስኪሆን የአማራ ሕዝብ የጦርነቱ ቦታ የትም ይሁን የት እስከ ዓላማው ፍፃሜ ድረስ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከወቅታዊው የክልሉ ሁኔታ አንፃር ሁለት የትኩረት አቅጣጫዎች መለየቱን የገለጹት ቢሮ ኃላፊው የኅልውና ዘመቻውን ዳር ማድረስ እና ነጻ የወጡ አካባቢዎችን መልሶ መገንባት የክልሉ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል፡፡ በጦርነቱ የደረሰው ምጣኔ ሃብታዊ ውድመት ከባድ በመሆኑ ነጻ የወጡ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ርብርብ እንዲያደርጉም የክልሉ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ለገቢ ማሰባሰቢያ ቀድሞ የተከፈቱ የባንክ ሒሳብ ደብተሮች አሁንም አገልግሎት ይሰጣሉ ያሉት አቶ ግዛቸው ከዚህ በተጨማሪም 9595 አጭር የጽሑፍ መልዕክት ተዘጋጅቷል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ መንግሥት በኅልውና ዘመቻው ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ምስጋና እያቀረበ በመልሶ ግንባታው ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በኅልውና ዘመቻው ወራሪው ቡድን ትልቅ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጸው ድሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ በግንባር መስዋእትነት ለከፈሉ፣ በቁሳቁስ ድጋፍ ላደረጉ፣ በኅልውና ዘመቻው ከኢትዮጵያ ጎን ለቆሙ እና ለጦርነቱ ደጀን ለሆነው ሕዝብ የክልሉ መንግሥት ያለውን አክብሮትም ገልጿል ብለዋል፡፡
ለተገኙ ድሎች፣ በግላቸው ጀብዱ ለፈጸሙ ጀግኖች እና የክብር መስዋእትነት ለከፈሉ የቁርጥ ቀን ልጆች የክልሉ መንግሥት በቀጣይ የእውቅና እና የምስጋና ሥነ ሥርዓት እንደሚያዘጋጅም ተጠቁሟል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleበኩር ጋዜጣ ታኅሣሥ 11/2014 ዓ.ም ዕትም
Next article“የሀገር ኅልውናን ለማስቀጠል ግንባር ድረስ በመዝመት ደማቅ የታሪክ ዐሻራ እያሳረፍን በመኾናችን ደስተኞች ነን” ዘማች የሕክምና ባለሙያዎች