
በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች ለወገን ጦር የደም ልገሳ ድጋፍም አድርገዋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ታራሚዎቹ በማረሚያ ቤት ቢገኙም ከሀገርና ከወገን የሚበልጥ የለም በሚል ነው ደማቸውን የለገሱት። “በሕግ ጥላ ስር ብንኾንም ስለ አማራነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት እናስባለን” ነው ያሉት።
ለወገን ጦር ደም በመለገስ አጋርነታቸውን ካሳዩት ታራሚዎች መካከል መንግሥቱ እያሱ ደማችን በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው የወገን ጦር አስፈላጊ በመኾኑ ደማችንን ለግሰናል ብሏል። አቅማቸው በፈቀደ መጠን ገንዘብ በማዋጣትም ለኅልውናው ዘመቻ አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን ታራሚው ተናግሯል።
ሌላዋ በሕግ ጥላ ስር የምትገኘው የሽወርቅ መላኩ ማረሚያ ቤት ብንገኝም የሀገራችን መደፈር አስቆጭቶናል ብላለች። መላው ሴቶች ወደ ግንባር በመዝመት፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ ደም በመለገስ ዘመቻውን ሊደግፉት እንደሚገባም ተናግራለች።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ማረሚያ ቤት መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ውብሸት መኮንን ታራሚዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነት ለወገን ጦር ደም ለግሰዋል ብለዋል። ደም መለገስ ብቻ ሳይኾን ከታራሚውና ከተቋሙ 580 ሺህ ብር ለወገን ጦር ለመለገስ ገንዘብ ማሰባሰባቸውን ኮማንደሩ ጠቁመዋል።
ታራሚዎቹ አቅማቸው በሚችለው ኹሉ ድጋፍ እያደረጉ መኾኑን አስረድተዋል። ታራሚዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነት ላደረጉት በጎ ተግባርም በማረሚያው ቤቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
