ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጮች መዘጋጀቱን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።

121

ታኅሣሥ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያዩበት መድረክ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ሌሊሴ ነሜ አስታወቁ።

ኮሚሽነሯ ባለፉት አራት ወራት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሐብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ኮሚሽነር ሌሊሴ እንዳሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጥሪ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያዩባቸው መድረኮች እየተዘጋጁ ነው።

መድረኮቹ በኢትዮጵያ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ያሉ አቅሞችን ማየት የሚያስችሉ እንደሆኑም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ዳያስፖራው መዋዕለ ንዋዩን ለማውጣትና በሀገሩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሳተፍ ሲመጣ የሚስተናገድበት ራሱን የቻለ ዴስክ መክፈቱንም ገልጸዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው በመምጣት በሀገር በቀል ኢንቨስትመንቶች ውስጥ እገዛ ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል መኖሩንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ዳያስፖራው ያልተነኩ የሀገሪቷን የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የውጭ ባለሃብቶችን ኢንቨስትመንቶችና ተያያዥ ሥራዎች እንዲጎበኝ ይደረጋል ብለዋል።

ኮሚሽነር ሌሊሴ በተጨማሪም ወደ ሀገር ቤት ያልገቡ የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በተለያዩ መንገዶች እያሳወቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ለዚህ ስኬትም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከዳያስፖራ ኤጀንሲና ከክልሎች ኢንቨስትመንት ቢሮዎች ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የተለያዩ ችግሮች ቢገጥሟትም በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት መጀመራቸውን ነው የገለጹት።

በአማራና በአፋር ክልሎች አሸባሪው ቡድን በከፈተው ጦርነት ሥራ አቁመው የነበሩ የኢንቨስትመንት መስኮችን በማስተባበር ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑንም ኮሚሽነር ሌሊሴ አስታውቀዋል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleየመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
Next articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ማረሚያ ቤት መምሪያ ለወገን ጦር ድጋፍ 580 ሺህ ብር ማሰባሰቡን ገለጸ፡፡