“የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና ሕዝብ ለአማራ ሕዝብ ያደረገው ድጋፍ የኢትዮጵያዊነት ነጸብራቅ ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

144

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የፍቅር ካባ የተጎናጸፈው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሕዝብና መንግሥት በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ለደረሰበት የአማራ ሕዝብ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን ገልጿል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጀዋር የተመራው ልዑክ በባሕር ዳር ተገኝቶ 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብና የአልባሳት እንዲሁም 5 ሚሊዮን ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለክልሉ መንግሥት አስረክቧል፡፡
ከንቲባው ‹‹ድሬዳዋን ወክለን የመጣነው ከክልሉ ጎን መሆናችንን ለማሳየት እና ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር ነው›› ብለዋል፡፡
ከጸጥታ ኀይሎች ጋር የአማራ ክልል ሕዝብና የጸጥታ ኃይል በመቀናጀት አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን #ለማጥፋት እያደረገ ባለው ተጋድሎ ኩራት እንደተሰማቸውም ገልጸዋል፡፡
ድሬዳዋ ላይ የጎርፍ አደጋ በተከሰተ ጊዜ የአማራ ክልል ሕዝብና መንግሥት ቀድሞ መድረሱን አስታውሰዋል፡፡ አሁንም የአማራ ክልል ሕግን ሲያስከብር የድሬዳዋ ሕዝብ በሚችለው አቅም የድርሻውን ለመወጣት የተደረገ ድጋፍ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ ተወላጆችና ደጋፊዎች ማኅበር አማካኝነት ድጋፍ መደረጉን በማስታወስም የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የሃይማኖት አባቶች እና አባ ገዳዎችም በክልሉ የደረሰውን ውድመት ለመመልከት ወደ አማራ ክልል አቅንተዋል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ለልዑካኑ በሰጡት ማብራሪያ ጠላት በወረራቸው አካባቢዎች ባደረሰው ግፍና መከራ ንጹሐን መገደላቸውን፣ በርካታ ሕዝብ መፈናቀሉን፣ ሀብትና ንብረት መውደሙን ገልጸዋል፡፡ ውድመቱን ለመተካት የተባበረ ጥረት እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡
የድሬዳዋ ሕዝብና መንግሥት አማራ ሕዝብን ችግር ለመካፈል በኢትዮጵያዊነትና በወንድማማችነት ስሜት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ‹‹እኛ ሁልጊዜ የምናምነው የአማራ ሕዝብ መጎዳት የኢትዮያ ሕዝብ መጎዳት ነው ብለን ነው›› ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡
የአማራ ሕዝብ ችግር ሲደርስበት ኢትዮጵያውያን ከጎናችን በመሆን ፈጥነው ለችግራችን ደራሽ መሆናቸው ደግሞ ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ የደረሰብንን ወረራ በጋራ መስዋእትነት ታግለን ጠላትን መደምሰስ መቻላችንም ሌላኛው ማረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት ምንጊዜም ኢትዮጵያዊነት የሕዝቡ መሰባሰቢያ ጥላ፣ የአብሮነት መገለጫና ችግርን በጋራ መፍቻ ቁልፍ መሣሪያ ነው፡፡ “የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና ሕዝብ ለአማራ ሕዝብ ያደረገው ድጋፍ የኢትዮጵያዊነት ነጸብራቅ ነው” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous article‟ድላችን ወሎን በማስለቀቅ ብቻ የሚለካ አይደለም“ በግንባሩ የክፍለ ጦር አዛዥ
Next articleበተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲደረግ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።