‟ድላችን ወሎን በማስለቀቅ ብቻ የሚለካ አይደለም“ በግንባሩ የክፍለ ጦር አዛዥ

280

ታኅሣሥ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር እና ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ በጀግንነት እየተወጡ መሆናቸውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የቀኝ እጆች፣ የክብር እና የሉዓላዊነት ዘቦች በኢትዮጵያ ላይ የተነሱትን ጠላቶች እየደመሰሱ በድል እየገሰገሱ ነው። የጀግኖች ስብስብ በኢትዮጵያ ላይ እጁን ያነሳውን የትግራይ ወራሪ እና አሸባሪ ቡድን ከአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ጋር በመቀናጀት እየደመሰሱት ነው። ጀግኖቹ በጠላት ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ነፃ በማውጣት ወደ ፊት እየተመሙ ነው። በስሜን ወሎ የነበረውን ጠላት የደመሰሱት የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት አሁንም ለሌላ ድል እየገሰገሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ የመከላከያ ሠራዊት አባል በመሆናቸው እና ሀገራቸውን በማገልገላቸው እድለኛ መሆናቸውን ነው የተናገሩት። ጠላትን ለማጥፋት ወደኋላ ሳንል እየገሰገስን የጠላትን ምሽግ ሰብረናል ብለዋል። ሠራዊቱ ምሽግ በመስበር እና ጠላትን #በመደምሰስ አስደናቂ ጀግንነት መፈፀሙንም ገልጸዋል። ግዳጅ በነበሩበት አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ አስደናቂ ደጀን መሆኑንም አስታውቀዋል። ሠራዊቱ እየጠነከረና ከድል ላይ ድል እየጨመረ እንደሚገሰግሰም ተናግረዋል።
ሠራዊቱ በቁጣ እና በወኔ ጠላትን ድባቅ እንደመታውም ነግረውናል። በጋሸና ግንባር በነበረው ግዳጅ መንግሥት እና ሕዝብ የሰጣቸውን ግዳጅ በጀግንነት መወጣታቸውንም ተናግረዋል። አስቸጋሪ የጠላትን ምሽጎችን በመስበር አካባቢውን ነጻ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ሠራዊቱ ፈንጅ እየረገጠ ምሽግ በመስበር የጠላትን ኃይል የደመሰሰ መሆኑንም በኩራት ተናግረዋል። ወደፊት ለሚሰጣቸው ግዳጅ የበለጠ እንደሚሠሩም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በእኛ በልጆቿ ትኮራለች ትከበራለችም ነው ያሉት። ሠራዊቱ የትኛውንም ችግር ተቋቁሞ ጠላትን የመደምሰስ አቅም እንዳለው አስረድተዋል።
በግንባሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የክፍለ ጦር የሬጅመንት አዛዥ ግዳጃቸው ጠላትን ድባቅ ለመምታት እንደነበር እና ግዳጃቸውን መወጣታቸውን ገልጸዋል። ከአማራ ልዩ ኀይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ ጋር በመሆን አስደናቂ ድል ማስገኘታቸውንም አስታውቀዋል።
በጀግና መሪዎች እና በጀግና ተዋጊዎች መናበብ ጠላትን ድባቅ እንደመቱትም ተናግረዋል። በሠራዊቱ ውስጥ አስደናቂ ጀግኖች እንዳሉም አመላክተዋል። ሠራዊቱ በጀግንነት ጠላትን በመደምሰስ ሕዝብ እንዲደሰት ማድረጉንም ገልጸዋል። ሠራዊቱ የጠላትን እና የተፈጥሮን ፈተና በመቋቋም ድል በድል መሆኑንም ጠቁመዋል። የሕዝብ ደጀንነት ከሚጠበቀው በላይ መሆኑንም አንስተዋል። ሕዝቡ ማዕበል ሆኖ በመነሳቱ ለሠራዊቱ ትልቅ ሞራል መሆኑንም አብራርተዋል።
ሠራዊቱ ለቀጣይ ግዳጅ ዝግጁ ነው ያሉት አዛዡ የውስጥ ጠላት ብቻ ሳይሆን የውጭ ጠላቶችም ቆም ብለው እንዲያስቡ አድርገን እንቀጣቸዋለን ብለዋል። ጠላትን እስከመጨረሻው ድረስ #ለመቅበር ዝግጁ ነንም ነው ያሉት።
አሸባሪው እና ወራሪው ቡድን ዜጎችን አሰቃይቷል፣ ይህን እያዬን ዝም አንልምም ብለዋል። የአማራ ልዩ ኀይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻው ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ለፈጸሙት ጀብዱ ምስጋና ይገባቸዋል፣ ጀግኖች ናቸውም ብለዋል።
በግንባሩ የክፍለ ጦር አዛዥ ሠራዊቱ የጠላትን ምሽግ እየሠበረ ጠላትን መድረሻ እንዳሳጣው ነው ያስታወቁት። ጠላት በተለያዩ ቦታዎች ከባድ ምሽጎች ቢሠራም የሠራዊቱን ግስጋሴ ግን ማስቆም እንዳልተቻለው ነው ያረጋገጡት። ሠራዊቱ የሚረማመደው በድል እንደሆነም ተናግረዋል። የኅብረተሰቡ ድጋፍ እና የተቀናጀው የሠራዊቱ ምት ጠላትን ተቀጥቅጦ እንዲወጣ እንዳደረገውም አስታውቀዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሰጡት መመሪያ መሠረት ጠላት ድባቅ መመታቱንም ተናግረዋል።
የሠራዊቱ ሞራል ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት አዛዡ ጠላት በሌሎች ግንባሮችም ትንኮሳ ሊፈፅም እንደሚችል ይገመታል፣ ሠራዊታችን የድል ሠራዊት ነው በየትኛውም ግንባር፣ የትኛውንም ምሽግ ሠብሮ ጠላትን ይደመስሳል ነው ያሉት።
ጠላት አይደለም በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በመነሻው በትግራይ ክልልም መኖር አይገባውም ብለዋል። ድላችን ወሎን በማስለቀቅ ብቻ የሚለካ አይደለም፣ ጠላት ከወሎ ከወጣ በኋላ ምን ሊያስብ ይችላል የሚለውን ማሰብ ተገቢ ነው፣ ስለዚህ በገባበት ገብቶ በማጥፋት ሕዝቡ ወደ ልማት እንዲዞር ማድረግ ይገባልም ብለዋል አዛዡ።
የተቆራረጠው የጠላት ኀይል ዳግም እንዳይነሳ አድርጎ ከምንጩ ድረስ ሄዶ መምታት ግድ እንደሚልም ተናግረዋል።
ሠራዊቱም ጠላትን ሙሉ ለሙሉ #ለማጥፋት ለሚሰጠው ግዳጅ ዝግጁ መሆኑን እና በጉጉት እንደሚጠብቀውም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleሕዝብን ከረሃብ እልቂት የታደገው የብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ አዋጅ በወልድያ ከተማ!
Next article“የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና ሕዝብ ለአማራ ሕዝብ ያደረገው ድጋፍ የኢትዮጵያዊነት ነጸብራቅ ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)