
ታኅሣሥ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጋር በተካሄደው ፍልሚያ በጀግንነት ተጋድሎ ያደረጉ የጸጥታ አካላት ለከፈሉት መስዋእትነት ትልቅ ክብር አለን ብለዋል። በግንባር ለተፋለሙ ጀግኖች አቀባበል ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ለአቀባበል በሚል የጥይት ተኩስ ማድረግ ማኅበረሰቡን ረብሿል ነው ያሉት። ጦርነቱ ገና አለማለቁን እና ትግሉ ቀጣይ መሆኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ በዚህ መልኩ አቀባበል በመደረጉ የክልሉ መንግሥት ደስተኛ አይደለም ብለዋል።
ጠላት ነገ ተመልሶ እንዳይወረን በጀግንነት እና በኃላፊነት መንፈስ ለመዋጋት ሁሉም መዘጋጀት ባለበት ወቅት ጥይትን ያለ አግባብ ማባከን ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መኾኑን ነው የተናገሩት። በመሆኑም በክልሉ ከአውደ ግንባር የሚመለሱ የጸጥታ ኃይሎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።
በግላቸውም ይሁን በመንግሥት የታጠቁትን መሣሪያ በቁጠባ በአግባቡ እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል።
ጦርነቱ ሳይጠናቀቅ ጥይትን ማባከን የሀገሪቱንም ይሁን የክልሉን ኢኮኖሚ ስለሚያዳክም በየትኛውም አካባቢ የሚመለስ ኃይል ጥይት መተኮስ እንዲያቆም አሳስበዋል።
መስዋእትነት ለከፈሉ የጸጥታ ኀይሎች ከፍተኛ አድናቆት አለን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የመጨረሻው ድል እስኪገኝ ጦርነቱ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
ከድል ማግስትም የጸጥታ ኀይሉ በሠራው ተጋድሎ ልክ እውቅና እንሰጣለን፤ ለመጪው ትውልድም እንዲታወስ እናደርጋለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
