በመጪዎቹ ጊዜያት የሚከበሩ በዓላትን በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከወገናቸው ጋር እንዲያሳልፉ ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ጥሪ አቀረቡ።

144

ታኅሣሥ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዓላቱን በአማራ ክልል እንዲያሳልፉ ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
መጪዎቹ ጊዜያት በኢትዮጵያ በዓላት የሚከበርባቸው በመሆኑ ዲያስፖራው ማኅበረሰብ በዓላቱን በሀገራቸው እንዲያሳልፉ የግብዣ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በቀጣይ ቀናት የሚከበሩ የልደት የጥምቀት፣ የቃና ዘገሊላ እና ሌሎች በዓላት በደስታና በፍቅር ከወገኖቻቸው ጋር እንዲያከብሩ ጋብዘዋል። ለዚህም ቤተሰቦቻችሁ እናንተን ለመቀበል በሚገባ ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
በሌላ በኩል አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በሁለቱ ክልሎች ንጹሐንን ገድሏል፣ በርካቶች ተፈናቅለዋል፣ በርካታ ሀብት አወድሟል፤ ዘርፏል ብለዋል። ይህንን በመገንዘብ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በውጪ ሆነው እየሠሩት ያለውን ወደር አልባ የዲፕሎማሲ ሥራ የበለጠ አጠናክረው እንዲሠሩ የሚያደርግ የቁጭት መንፈስ እንደሚያገኙም አስገንዝበዋል።
ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ያላቸውን ሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ በመመንዘር በአንድ በኩል የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ የተዳከመውን ምጣኔ ሃብት በማነቃቃት፣ አቅማቸው የሚፈቅድ ደግሞ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ በማቋቋም፣ የወደመውን መሠረተ ልማት መልሶ በመገንባት ሂደቱ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉበት ወቅት እንደሆነ ተናግረዋል።
በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥሪውን ተቀብለው ከወገናቸው ጋር እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል። ጉብኝትና ውይይቶችን በማድረግ በቀጣይ የሀገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ላይ እያንዳንዱ ግለሰብ ሊያደርግ በሚችለው አስተዋጽኦ ላይ እንወያያለን ብለዋል። በተመሳሳይ በዲያስፖራው ተሳትፎ የክልሉን ኢንቨስትመንት በምን አግባብ ማስፋፋት እና የሕዝቡን ሕይወት መቀየር እንደሚቻል ገንቢ ውይይት ይደረጋል ነው ያሉት።
በጥር ወቅት ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት በተለይ በአማራ ክልል በድምቀት ይከበራሉ ብለዋል። በዓሉን ስናከብር በአንድ በኩል የወገን ጦር ባስመዘገበው አኩሪ ድል እየተደሰትን፣ ለዚህ ያበቁንን ጀግኖች እያመሰገንን እና በሽብር ቡድኑ የደረሰውን ውድመት በመመልከት የምናከበርው በመሆኑ የዲያስፖራው አባላት ዘርፈ ብዙ ተልዕኮ ይዘው ወደ ሀገራቸው እንደሚገቡ ነው የተናገሩት።
ወልድያ፣ ደሴና ኮምቦልቻን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎችም ልዩ ልዩ ሁነቶች እንደሚዘጋጁ አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለዲያስፖራ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous article“በአሸባሪው ቡድን በደረሰው መጠነ ሰፊ ውድመትና ዝርፊያ የተጎዳውን ሕዝባችን ለማቋቋም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ ያስፈልጋል” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
Next article“ሁሉም ለቀጣይ ትግል መዘጋጀት ባለበት ወቅት ጥይትን ያለ አግባብ ማባከን ኀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)