‹‹ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ሳይሆን ቀድሞ ችግሩን ለይቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡›› አስተያዬት ሰጭዎች

158

ባሕር ዳር፡ መስከረም 24/2012 ዓ/ም (አብመድ) ሰሞኑን በማዕከላዊ ጎንደር አካባቢ በተፈጠረ የሠላም መደፍስ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረትም ወድሟል፡፡ በጠፋው የሰው ሕይወት እና በወደመው ንብረት ማዘናቸውን የአማራ ክልል የጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀ መንበር አቶ ዳኝነት አያሌው ገልጸዋል፡፡

አቶ ዳኝነት ‹‹ሰሞኑን እየተፈጠረ ያለው ጉዳይ አሳዛኝ ነው፡፡ ቅማንት እና አማራ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተለያይተው አያውቁም፤ የተጋባ የተዋለደ፤ በደም የተሳሰረ ሕዝብ ነው፡፡ ይሁን እንጅ የኢትዮጵያን አንድነት የማይወዱ ኃይሎች አንድ ሆነው የኖሩትን ሕዝቦች ለመከፋፈል፤ ልማቱም እንዲደናቀፍ፤ ፀጥታውም እንዲደፈርስ ለማድረግ የሚሸርቡት ሴራ እያጋጨው ነው›› ብለዋል፡፡

የአማራ እና የቅማንት ሕዝቦች ለቅጥረኞች ቦታ ሳይሰጡ እና ክፍተት ሳይፈጥሩ አንድነታቸውን አጠናክረው መኖር እንዳለባቸውም ሊቀ መንበሩ መክረዋል፡፡ ‹‹አማራ እና ቅማንት አንድ ናቸው፤ የአንድ እናት ልጆች፤ ወንድማማቾች እንዲጣሉ ሲደረግ መንቃት ያስፈልጋል፤ እንድነታቸውንም ማጠናከር አለባቸው፤ የአማራ ሕዝብ ሠላሙን ነቅቶ መጠበቅ አለበት፤ ወጣቱም እየተሠራ ያለውን ሴራ በመገንዘብና መንቃት ይኖርበታል›› ብለዋል አቶ ዳኝነት ለአብመድ ሲናገሩ፡፡

በሁለቱ ሕዝቦች መካከል እየገባ ልዩነት የሚፈጥረውን ወጣቱ መቀበል እና በስሜት መነዳት እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሙዚየም አስጎብኝ አቶ አበበ ማሞ ደግሞ ‹‹ድርጊቱ የሚያሳዝን ነው፤ ሕዝቡ የአባቶቹን ታሪክ ሊደግም ይገባዋል እንጅ እርስ በርሱ የሚጋጭ መሆን የለበትም› ብለዋል፡፡ ‹‹ከሦስት ዓመት ወዲህ እየሆነ ያለው ነገር አሳዝኖናል፤ የሰው ልጅ እየተጎዳ መሆኑን ስንሰማ ስሜታችንን ነክቶታል፤ አካባቢው በታሪክ የምንኮራበት ነው፤ እንዲህ በታሪክ የምንኮራበት አካባቢ ዛሬ እንዳለው አካባቢ መሆን የለበትም፤ በመሆኑም አካባቢው የአባቶቹን እና የቅድመ አያቶቹን ታሪክ ይዞ ነው መጓዝ ያለበት›› ብለዋል፡፡

‹‹ሕዝቡ የቅድመ አያቶቹን ለሀገር አሳቢነታቸውን፣ ተቆርቋሪነታቸውን፣ ለሀገር መሞትን ሊወርስ ይገባዋል›› ያሉት አቶ አበበ አባቶች ለሀገር የሚሞቱ እንጅ ወንድማቸውን የሚያጠፉ እንዳነበሩ፣ እነ ዓፄ ቴዎድሮስ ወንድም ማጥፋትን ሳይሆን ለሀገራቸው ልጆች ሲሉ ራሳቸውን የሚሰው እንደነበሩ፤ አሁን ያለው ትውልድም ከዚህ ተምሮ እርስ በርስ መጠፋፋትን ሳይሆን በጋራ ሆኖ ሀገርና ሕዝብን ከጠላት መታደግን እንዲያስቀድም መክረዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢዋ የሀገር ሽማግሌዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንንም በድርጊቱ እንዳዘኑ ተናግረዋል፡፡ በሕዝብ ስም የፖለቲካ ጥቅመኞች አብሮ የኖረን ሕዝብ እርስ በርስ ለማናቆር በሚያደርጉት ጥረት ንጹኃን ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ንብረታቸው ሲወድም ማየትና መስማት አሳዛኝ መሆኑን የተናገሩት ሊቀ ኅሩያን በላይ የሰው ልጅ ባለው አጭር ዕድሜ በጎ ነገርን ሰርቶ ማለፍ ትልቅ ነገር መሆኑን እንዲረዳና እርስ በእርስ እንዲረዳዳ አሳስበዋል፡፡

‹‹በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የታሪክ ጠባሳ መተው የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል›› ያሉት ሊቀ ኅሩያን በላይ ሕዝቦችን ለሚያጫርስ ጉዳይ ሕዝቡ እንዳይተጋ ተማጽነዋል፡፡ ‹‹እየተፈጠረ ያለውን ነገር አቁሞ ይቅር ተባብሎ ወደ ሠላም መምጣት ይገባል፤ ጦርነት የሚያመጣው ውድቀት፣ ሞት፣ ችግር፣ ጥላቻ እና የታሪክ ጠባሳ እንጅ በጎ ነገር ስለሌለ ሕዝቡ ቆም ብሎ ራሱን ሊያይ ይገባዋል›› ብለዋል፡፡
መንግሥት ችግሩን በሚፈጥሩ አካላት ላይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባው ያሳሰቡት አስተያዬት ሰጭዎቹ ነገሮች አድገው ከመበላሸታቸው በፊት የዕለት ከዕለት ክትትል እያደረገ ችግሮችን ማስወገድ እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል፡፡

ሕዝብ ለማጋጨት ዓላማ እየተቀበለ እየመጣ ችግር የሚፈጥረው አካል ጊዜ ሳይሰጠው ሕጋዊ ርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ አሁንም የችግሩ መፍቻ ቁልፍ ያለው መንግሥት መሆኑን ያመለከቱት አስተያዬት ሰጭዎቹ ሕዝቡ የራሱ ድርሻ ቢኖረውም መንግሥት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ ሥራ መሥራት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱም ቢሆን በወንድማማቾች መካከል ጣልቃ እየገቡ እንዲህ ዓይነት እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን የመለዬት እና ለሕግ የማቅረብ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባና አስቀድሞ ሁኔታዎችን የመተንበይ የመቆጣጠር ሥራ እንዲያከናውን አሳስበዋል፡፡

አዘጋጅ፡- ምሥጋናው ብርሃ

Previous articleየታጠቁ አካላት በኤፍራታና ግድም ወረዳ ተኩስ ከፍተው አካባቢውን ለመረበሽ ያደረጉት ሙከራ መክሸፉን የወረዳው አስተዳድርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
Next article“የትኛውም ሕዝብ ኃላፊነት በጎደላቸው መገናኛ ብዙኃን ጥቃት እንዲደርስበት አንፈልግም፤ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድም እናደርጋለን።” የብሮድካስት ባለሥልጣን