
በምስጋና ዝግጅቱ የወገን ጦር ላደረገው ተጋድሎ እውቅናና ለቀጣይ ግዳጅም ተልእኮ ይሠጣል ተብሏል።
ታኅሣሥ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጋሸና ግንባር ጠላትን ድባቅ ለመታው የወገን ጦር የምስጋና ዝግጅት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዝግጅቱም የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የወገን ጦር ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት በጋሸና ግንባር የነበረውን ጠላት በመደምሰስ አካባቢውን ነፃ ማውጣቱ ይታወሳል። ጥምር ጦሩ ጠላትን እየደመሰሰ የቀረውንም እግር በእግር እየተከታተለ እየቀበረ ነው። የወገን ጦር ለፈጸመው ጀግንነት ነው በጋሸና የምስጋና ዝግጅት የተደረገለት።
በምስጋና ዝግጅቱ የሰሜን ምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና መንግሥት እና ሕዝብ የሰጠንን ተልዕኮ በተሳካ ሁኔታ በመፈፀማችን ደስታ ተሰምቶናል ነው ያሉት። ባነሱ በቆሸሹ፣ በዘመናት የተለያየ ትውልድ በጨረሱ የኢትዮጵያ ደመኛ ጠላቶች ሀገራችን ክፉኛ ተጠቅታ በሕይወት፣ በንብረትና በሥነልቦና ብዙ ችግር ደርሶባታል ብለዋል። በተወጠረ እብሪታቸው ሊያንበረክኩን ቢሹም ሠራዊቱ በተሰጠው ግዳጅ ድባቅ እንደመታቸው ገልፀዋል።
ጠላት በጋሸና ግንባር ምሽግ ቆፍሮ፣ ንብረት ሲዘርፍና በደል ሲፈፅም መቆየቱን ያነሱት አዛዡ የጠላትን ኃይል በመደምሰስ እንዳይመለስ አድርገው መቀጣቱን ተናግረዋል። ለጥፋት የተሰለፈውን ጠላት በመደምሰስ ተልእኳቸውን መፈፀማቸውንም አስታውቀዋል።
ጠላትን በመደምሰስ በአጭር ጊዜ ቀጣናውን ነፃ ለማውጣት በተደረገው ፈጣን ማጥቃት በጋሸና የነበረው የጠላት ኃይል መደምሰሱንና በዚህም ሌሎችም አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ነፃ መውጣታቸውን ነው የተናገሩት።
መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሻ ጋር በመቀናጀት አመርቂ ድል ማስመዝገቡንና አቅሙን ማሳየቱንም አስታውቀዋል። ሠራዊቱ ሀገርን ከብተና መታደጉንና ጠላትን ማሳፈሩንም ገልፀዋል። የሠራዊቱ አባላት ላሳዩት ጀግንነት እና ጀብዱም አመስግነዋል። ሠራዊቱ ብርቱና የፀና ጀግንነት ማሳየቱንም አውስተዋል። የወገን ጦር ምንም ሳይሳሳ ጠላትን በመደምሰስ ለሕዝብ እፎይታ መሰጠቱንም ተናግረዋል። ፈንጅ ረግጦ ምሽግ መስበርና ወገን እንዲገሰግስ የማድረጉ የጀግንነት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋልም ነው ያሉት።
ወደ ፊትም ሀገርና ሕዝብ የሰጠንን ተልዕኮ በጀግንነት እንፈፅማለን፤ አኩሪ ታሪክ ለመሥራት ሁሌም ዝግጁ ነንም ብለዋል። ለተገኘው ድል ደጀኑ ሕዝብ ስንቅ በማቀበል፣ በማዋጋትና ዘርፈ ብዙ ድጋፍ በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነቱን በመወጣቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ለአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሻም ለፈፀሙት ጀብዱና ተልእኮ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ነው ያሉት።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
