በአማራ ክልል የሚገኘውን እምቅ ሀብት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የወደመውን ሀብት መተካት እንደሚቻል የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ፡፡

192

እንጅባራ፡ ታኅሣሥ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጃዊ ወረዳ ወጣቶችና ባለሀብቶች የቆላ ስንዴን በማልማት ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ ለማስቀረት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የበኩላቸውን እገዛ እያደረጉ ነው። ወጣቶቹና ባለሀብቶቹ የጣና በለስ የስኳር ፋብሪካ የሰጣቸውን ጊዜያዊ መሬት በመጠቀም የቆላ ስንዴን እያለሙ ነው።
የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ የስኳር ፕሮጀክቶች ለጊዜው የማይጠቀሙበትን መሬት ወደ ቆላ ስንዴ ልማት ማስገባት እንደተቻለ ጠቁመዋል። የቆላ ስንዴን ለማልማት የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ትልቅ ትብብር በማድረጋቸው ሚኒስትሯ አድንቀዋል።
በምልከታቸው ወቅት የአማራ ክልል ባለሀብቶች እና ወጣቶች ወደ ቆላ ስንዴ ልማት መግባታቸውን እንዳዩ የተናገሩት ኢንጂነር አይሻ የስኳር ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅማቸው ማልማት እስኪጀምሩ ድረስ የስንዴ ልማቱ ይቀጥላል ብለዋል።
“የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በሙሉ አቅሙ ማልማት ቢጀምርም የቆላ ስንዴን ለሚያለሙ ባለሀብቶች እና ወጣቶች 20 ሺህ ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል” ብለዋል።

በአማራ ክልል የሚገኘውን እምቅ ሀብት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የባከነውን ሀብት መተካት እንደሚቻል ሚኒስትሯ አመላክተዋል። “ከተበጣጠሰ የመሬት አጠቃቀም በመውጣት ወደ ተቀናጀና ሜካናይዝድ ወደኾነ የግብርና ሥራ ቢገባ እጃችንን ሊጠመዝዙን የሚፈልጉ አካላት ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል” ብለዋል።
የጣና በለስ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂነር ጌታቸው አስማረ የጣና በለስ ፕሮጀክት ለስኳር ልማት፣ ለቆላ ስንዴ ልማት፣ ለቅባት እህሎች እና ሌሎችንም ለማልማት እምቅ ሀብት አለው ብለዋል። ፕሮጀክቱ በአግባቡ ሥራ ላይ ቢውል ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርት ያስቀራል፣ የዜጎችንም ሕይወት ይቀይራል ነው ያሉት።

የቤአኤካ ኀላፊነቱ የተወሰነ የንግድ ማኅበር ተወካይ አቶ መልሰው ዳኘ በተሰጣቸው የቆላ ስንዴ ማልሚያ መሬት የሚጠበቅባቸውን ሥራ በአግባቡ እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል። ማኅበራቸው ትልቅ የማልማት አቅም ስላለው መንግሥት ተጨማሪ መሬት እንዲሰጣቸውም ተወካዩ ጠይቀዋል። አሁን ላይ 480 ሄክታር መሬት ላይ የቆላ ስንዴን እያለሙ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ መልሰው ማኅበራቸው 40 ሺህ ሄክታር ድረስ በማልማት ሀገርን የማሳደግ አቅም አለው ነው ያሉት።
የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት የማኅበራቸውን እንቅስቃሴና ችግር በመለየት መፍትሔ ይሰጣል ብለው እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል። በርካታ ወጣቶችም በመደራጀት በጣና በለስ የቆላ ስንዴን እያለሙ ይገኛሉ።

የጣና በለስ የወጣቶች መስኖ ልማት ማኅበር ተወካይ ደሳለኝ ዓለማየሁ መንግሥት ዘላቂ የሆነ የስንዴ ማልሚያ መሬትን እንዲሰጣቸው ጠይቋል። በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የአገዛዝ ዘመን የመሬቱ ተጠቃሚ እንዳልነበሩ የተናገረው ወጣቱ አሁን ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸው እራሳቸዉንም ሆነ ሀገራቸውን ለማሳደግ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድቷል።
የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኀላፊ ዳኛቸው ፈንታ (ዶክተር) የአማራ ክልል 360 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ሊለማ እንደሚችል ጠቁመዋል። አሁን ያሉት ፕሮጀክቶች ሙሉ የማልማት አቅማቸውን ቢጠቀሙ እንኳን መልማት የሚችለውን የሄክታር መጠን የሚያለሙ እንዳልሆነ አመላክተዋል። ስለሆነም የክልሉን የመስኖ ልማት አቅም አሟጥጦ ለመጠቀም የፌዴራሉ እና የክልሉ መንግሥት በቅንጅት መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ – ከጃዊ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ!!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

Previous article”ጥልቅ ጉድጓድ ከሞት ላያስጥላቸው፣ መቆፈሩ ተረፋቸው”
Next articleበጋሸና ግንባር ጠላትን ድባቅ ለመታው የወገን ጦር የምስጋና ዝግጅት እየተካሄደ ነው፡፡