”ጥልቅ ጉድጓድ ከሞት ላያስጥላቸው፣ መቆፈሩ ተረፋቸው”

347

ታኅሣሥ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ለማሸነፍ፣ በድል ለማለፍ፣ ለነፃነት፣ ለሉዓላዊነት ጥልቅ ጀግንነት እንጂ ጥልቅ ጉድጓድ ብቻ በቂ አይደለም። በጥልቅ ምሽግ ውስጥ የሚያድር ጥልቅ ልብ ያለው፣ ጀግንነት የተቸረው፣ ልበ ሙሉነት ያስፈልጋል። በጥልቅ ምሽግ ላይ ደንዳና ልብ ያለው ሠራዊት ሲጨመርበት እቅዱ ይሰምራል፣ ድሉ ያምራል። ያለ ልብ መሣሪያ ከንቱ ነው፣ ምሽግም ከንቱ ነው፣ ለማጥቃት የቆፈሩት ምሽግ ለመቃብር ይሆናል። አይጦች በጠለቀ ጉድጓድ ውስጥ ይኖራሉ። የጠለቀ ልብ፣ የተባ ጀግንነት ስሌላቸው ከጉድጓዳቸው በር የደረሰው ሁሉ ይገድላቸዋል። የጠለቀ ጉድጓድ ቢኖራቸውም ድመትን ግን አሸንፈው አያውቁም። ከጉድጓዱ ብቅ ባሉ ቁጥር እየታነቁ ያልቃሉ። እንደ ጉድጓዳቸው ጥልቀት የጠለቀ ጀግንነት ቢኖራቸው ግን የሚደፍራቸው ባልኖረ ነበር።
የኢትዮጵያ ጀግኖች ሀገሬ ተነካች ብለው ካመረሩ፣ የሚያቆማቸው ነገር አይኖርም፣ አልተፈጠረምም፣ ወደፊትም አይፈጠርም። እውነት፣ መገፋት፣ ጀግንነት እና አንድነት ከእነርሱ ጋር ናትና ድል የራሳቸው ነው። አሸናፊነት መገለጫቸው ነው።
ኢትዮጵያውያን ጦርነት ሲገጥሙ እንደሚያሸንፉ እርግጠኞች ናቸው፣ እነርሱን የሚያሳስባቸው መቼ እንጨርሰው፣ መቼስ ድሉን እናብስረው የሚለው ነው እንጂ አሸንፈው እንደሚመጡ፣ በድል እንደሚወጡ የኢትዮጵያን ስም ሲጠሩ፣ በሠንደቁ ግርጌ ሲማማሉ ያውቁታል።

እነርሱ ተቆጥተው ሲነሱ፣ አልመው ሲተኩሱ፣ በጀግንነት ሲገሰግሱ አጀብ እያሉ ከማድነቅ በስተቀር ምን ይባላል? ማንስ ችሎ ቁሙ ይላቸዋል? እነርሱን ማስቆም አይቻልም፤ የሚያቆማቸው ማሸነፍ ብቻ ነውና። ኢትዮጵያውያን ተራራዎችን አቋርጠዋል፣ ሸንተረሮችን ተሸጋግረዋል፣ ምሽጎችን ደርመሰዋል፣ በጠላት ሰፈር በልበ ሙሉነት ተረማምደዋል፣ የበረሃውን ወበቅ፣ የደጋውን ቁር ተቋቁመዋል፣ ረሃብና ጥሙን፣ ድካምና ችግሩን ችለዋል፣ ሲሻቸው ማርከዋል፣ ጠላትን እንደ ቆሎ ጨብጠዋል፣ ሲሻቸው ግዳይ በግዳይ አድርገዋል። ግዳያቸውን እየተረማመዱ ፎክረዋል፣ ሸልለዋል። አንበሳ ገዳይ እያሉ ዘፍነዋል። ኢትዮጵያን ለመውጋት፣ ኢትዮጵያውያንን ለማጥፋት በጠላቶች የተሠሩ ምሽጎች ሁሉ በየዘመናቱ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ተደርምሰዋል፣ ፈርሰዋል፣ ተሰብረዋል፣ የጠላት ቅስሙ ብቻ ሳይሆን አጥንቱም ይሰበራል፣ ሕይወቱም በምሽጉ ዙሪያ ይቀራል።
የኢትዮጵያውያንን ክንድ የሚቋቋም የጠላት ምሽግ እስካሁን አልተሠራም፣ ወደፊትም አይሠራም። ወደ መሬት ቢጠልቅ፣ ወደ ሰማይ ቢመጥቅ ከመፍረስና ከመገርሰስ አይተርፍም። ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ምሽግ ተቆፍሮባታል፣ ጦር ዘምቶባታል፣ ጦርነት ተከፍቶባታል፣ እርሷም ጦሩን ደምስሳለች፣ ምሽጉን አፍርሳለች፣ ጦርነቱን በድል ተወጥታለች። ጥቁር ሁሉ የሚመካበት፣ በየሄደበት ሁሉ የሚኮራበት፣ የሚከበርበት ታሪክ የሠራችው ኢትዮጵያ ከምሽግ ምሽግ እየተራመዱ ጠላትን በሚደመስሱ ጀግና ልጆቿ ነው። ተዋርዶ ከመሰንበት፣ ተከብሮ መሞት ይሻላል በሚለው ብሂላቸው፣ የክብር ሞት እየሞቱ፣ ጠላታቸውን አሳምነው እየመቱ ነፃ ሀገር አውርሰዋል። የጠላትን የክፋት ተራራ ሁሉ ገርስሰዋል።
”ከምሽግ ምሽግ ተራምዶ፣ አቆላላፊ የሬሳ ነዶ” የተባለላቸው ጀግኖች ከምሽግ ምሽግ እየተራመዱ፣ ጠላትን እያርበደበዱ የሚደቁሱ ናቸው፣ የሚሰጉት ምሽግ አይገኝም። ሁሉንም በጀግንነት ይሻገሩታል፣ እንዳልነበር ያደርጉታል። የሚጋረፈውን የፊታቸውን ግለት ማን ይችላል? እየነጠለ የሚጥለውን አፈሙዛቸውን ማን ይቋቋማል? ክንዳቸው አይዝልም፣ ማንጠሪያቸው አይስትምና እያነጠሩ ይጥሉታል፣ ተመልከት እያሉ ይነጥሉታል። ”አይቆረጠም የደንጋይ ቆሎ አይወረወር የእሳት አሎሎ ፍቅሩን ነው እንጂ ጠቡን ማን ችሎ” የተባለለት የኢትዮጵያ ጀግና ፍቅሩን እንጂ ጠቡን የሚችለው የለም። ሲያፈቅር ልቡን ይሰጣል፣ እስከ ሞት ይታመናል፣ ከራስ በፊት ለታመነለት ዓላማ ይላል። ቃሉን አያብልም። ሲያምን እስከመጨረሻው ነው። ፍቅሩ ልክ የለውም። ከተጣላ ግን የሚችለው የለም። ሲያምን ከከዱት፣ ሲደግፍ ከገፉት፣ ሲታመን ከካዱት፣ ሲጠብቃቸው ከጀርባው ከወጉት፣ ሲሞትላቸው ከገደሉት፣ እመነቱን ካጎደሉበት ግን አይቻልም። ጠቡን የሚችል የለም። ባመነው ልክ ይቆጣል፣ በእምነቱ ልክ ይቀጣል።

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በፈፀመው ወረራ በሚደረጉ አውደ ውጊያዎች በተለያዩ አካባቢዎች የማየት እድሉ ገጥሞኛል። የፈፀማቸውን በደሎች አይቻለሁ፣ ያደረሰውን ግፍ ታዝቤያለሁ፣ የደረሰበትን ኪሳራም ተመልክቻለሁ። ባየኋቸው ኹሉ የተለያዩ ስሜቶች ተሰምተውኛል።
ከሰሞኑ በሰሜን ወሎ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ቡድኑ የተመታበትን፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች ጀብዱ የሠሩበትን፣ የኢትዮጵያውያን ክብርና አንድነት የታየበትን ሥፍራዎች ተመልክቻለሁ። በእነዚህ ሥፍራዎች የሽብር ቡድኑ ለወራት የቆፈራቸው በሰው ቁመት ልክ ምሽጎችን ሠርቷል። በቆፈረው ጥልቅ ምሽግ በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን አከማችቷል። በምሽጎቹ ጥልቀት ተኩራርቷል፤ ተመክቷል፣ ይህን ምሽግ የሚራመድ፣ ችሎ የሚንድ አይገኝም ሲልም ዝቷል። ዳሩ ምሽጎቹ ለወራት ተቆፍረው ያዋጉት ግፋ ቢል ለቀናት ፣ ካለበለዚያ ለሰዓታት ነበር። እንዴት? ካሉ በጥልቁ ምሽግ ውስጥ የጠለቀ ጀግንነት አልነበረም። በጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ የነበረው እብሪት፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ጨለምተኝነት፣ ስግብግብነት ነውና። እነዚህ ደግሞ በተሰባሰቡበት ጉድጓድ ይቀራሉ እንጂ ከእውነት እና ከጀግንነት ጋር ተዋግተው አያሸንፉም። የጠለቀ ጀግንነት ያለውን የጠለቀ ጉድጓድ የቆፈረው ጠላት አያድነውም። ሆኖለት አይመክተውም።
መከላከያው ሲበር፣ ልዩ ኃይሉ ሲወረወር፣ ሚሊሻው ሲሰግር፣ ፋኖው ሲንደረደር በጥልቁ ምሽግ ውስጥ የነበሩት ተጨነቁ፣ ላብ አጠመቃቸው፣ መውጫው ጠፋባቸው፣ ሰማይ ተደፋባቸው፣ የጀግኖች ግለት ገረፋቸው፣ የጀግኖች ትንፋሽ ጣላቸው፣ የተመኩበት ምሽግ ከዳቸው፣ ሁሉም እንዳልነበር ኾነ። ጀግኖቹ እየገሰገሱ በዚያ ምሽግ ደረሱ። በጉድጓድ ውስጥ ያለው አፈር አለበሱ። የተወለዱበትን ቀን ረገሙ፣ በጀግኖቹ ፍጥነት ተገረሙ።

አሸባሪው ቡድን በመጨረሻው ዘመን ተንኮለኞች ጉደጓዳቸውን በራሳቸው ጭረው ይሞታሉ እንደሚባለው ሆኖበታል። በጫረው ጉድጓድ ተቀብሯል፣ በቆፈረው ምሽግ ተዳፍኗል። ረጃጅም ምሽጎች፣ በጥልቀት ተቆፈረው ነበር፣ ነገር ግን አሁን እንዳልነበር ኾነዋል። ያን ምሽግ ያየ ኹሉ በጀግኖች ገድል መደመሙ አይቀርም። ምን አይነት መሰጠት ነው? ምን አይነት ጀግንነት ነው? ምን አይነት የሀገር ፍቅር ነው? ምን አይነት የሀገር ክብር ነው? እንዲህ ያደረጋቸው፣ እንዲህ ያጀገናቸው ማለቱ አይቀርም። እነርሱ የሚሰስቱት ምንም ነገር የላቸውም። ኹሉንም ነገር ለሀገራቸው ይሰጣሉ። ጠላቶች ጥልቅ ጉድጓድ ከሞት ላያስጥላቸው፣ መቆፈሩ ተረፋቸው ። የተረፋቸው መቆፈሩና መድከሙ ብቻ ነው። ሞታቸውን ያዘገየ ጉድጓድ፣ ድል ያመጣላቸው ምሽግ አልተገኘም። ኹሉም ከሞት አላዳኗቸውም። ተሸንፎ ከመመለስ፣ አፍሮ ከመሄድ አልታደጓቸውም፣ ማን ይደፍረናል ያሉት ተደፍረዋል፣ ማን ይነካናል ያሉት ተንኮታኩተዋል፣ ግስጋሴያችንን የሚያስቆም የለም ያሉት በሀፍረት ቆፈን ውስጥ ተቀምጠዋል፣ ጀግንነታችን እዩልን ያሉት ድረሱልን ብለዋል፣ ኹሉም ነገር በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፣ ትጥቃቸው በማይፈታው ጀግኖች እንዳልነበር ኾኗል።
አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ አስቀድሞ፣ ኢትዮጵያ እያለ የሚገሰግሰውን፣ ተመልከት እያለ የሚተኩሰውን ጀግና ማን ያቆመዋል? ምሽጉን እንደተራመዱት፣ እንዴት እንደሰበሩት፣ ጠላትን እስኪበቃው ድረስ እንዴት እንደመቱት ባሰብኩ ቁጥር በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለው ጀግንነት፣ ቁርጠኝነት፣ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለው አትንኩኝ ባይነት ያስደንቀኛል። ያስደምመኛል። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለውን ምስጢር የሚፈታው፣ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለው ጀግንነት የሚረታው፣ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለውን አንድነት የሚሰብረው፣ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለው ክብር የሚያዋርደው ጠላት አይገኝም።
ለዚህ ደግሞ በሰሜን ወሎ ዞን የተሰበሩ ምሽጎች፣ እንደ ቅጠል የረገፉት ጠላቶች ምስክሮች ናቸው።
መነሻው ከየትም ይሁን ኢትዮጵያን የነካ ጠላት ሁሉ መጨረሻው አለመኖር መኾኑን ምሽጎቹ ይመሰክራሉ። አንደበት ቢኖራቸው የሠራዊቱ ጀግንነት ይናገራሉ። ያን ያየ ኹሉ እናንተ ተራራዎች፣ እናንተ ሸንተረሮች የጀግኖችን ታሪክ አስፍሩ፣ የውጊያውን ውሎ ዘርዝሩ፣ በወርቅ ቀለም ፃፉት፣ በማያረጅ ብራና ላይ አስፍሩት። ያያችሁትን ለዓለም ንገሩ። የጀግኖችን ገደል ዘምሩ ይላል። እኔም በጥልቀት የተቆፈሩትን ምሽጎች አፍ አውጥተው ይነግሩኝ ይመስል አፈጠጥኩባቸው፣ ያዩትን ጀግንነት እንደሚነግሩኝ ኹሉ በአግራሞት አየኋቸው። እኔ በጀግኖቹ ኮርቻለሁ፣ በጀብዳቸው ተደምሜያለሁ፣ ግድብ የሚሠራበት እንጂ ጠላት የተደበቀበት በማይመስለው ምሽግ ውስጥ ተራምደው፣ ጠላትን አርበድብደው ባዶ በማድረጋቸው ተገርሜያለሁ። ለኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ጀግንነት ልክ የለውም። ወሰን አይገኝለትም። እንዲያው ብቻ እፁብ ማለት ይሻላል እንጂ።
ወዳጄ አንተም አድንቃቸው፣ ጀግኖችን እያቸው፣ ተከተላቸው፣ እነርሱን ምሰላቸው፣ ስትመስላቸው ታሪክ ትሠራለህ፣ ሀገር ታከብራለህ፣ ነፃነትን ታስከብራለህ፣ ጠላትህን ታሳፍራለህ፣ አሁን የጠላት ቅስም እንደ ምሽጎቹ ተሰብሯል፣ የጀግኖች ልብ ግን እንደ አለት ደንድኗል። ወኔያቸው ግሏል፣ ወደፊት እየገሰገሱ ነው ። እኛም እንከተላቸዋለን።
በታርቆ ክንዴ

Previous article‹‹መንገድ ሲመሩ የነበሩ የውስጥ ባንዳዎችን ወደ ሕግ ማቅረብ ተጀምሯል››
Next articleበአማራ ክልል የሚገኘውን እምቅ ሀብት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የወደመውን ሀብት መተካት እንደሚቻል የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ፡፡