
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ባስተላለፉት መልዕክት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የፈጸመው ወረራ የአማራ ሕዝብ ለዓመታት ያፈራውን ሀብት በመዝረፍ፣ ተቋማቱን በማውደም፣ በማፈራረስ እና ሕዝቡን በመጨፍጨፍ አንገት ለማስደፋት እንዲሁም የኢትዮጵያዊነትን መሠረትም ለመናድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ወንበዴዎች እንዲሁም በሚደግፏቸው የውጪ ጠላቶች በአማራ፣ በአፋር እና በኢትዮጵያዊያን ላይ ጦርነት ቢከፍቱም አሸናፊነትን በትውልድ ቅብብሎሽ ይዘው የተጓዙት ኢትዮጵያውያን ዛሬም አሸናፊ ሆነዋል ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ፡፡
ዶክተር ይልቃል እንዳሉት ኢትዮጵያውያን ሌላን ሀገር ለመውረር የተሰለፉበት የታሪክ አጋጣሚ የለም፤ ገፍቶ ለመጣ ግን ምሕረት የላቸውም፡፡ በታሪካቸው የተሸነፉበት የጦር ግንባር ውሎ እንደሌለም አስታውሰዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድም መስዋእትነት በመክፈል የሀገራቸውን ሕልውና፣ ክብራቸውን እና ሕልውናቸውን በማስጠበቅ የማይደፈሩ መሆናቸውን በድጋሜ አስመስክረዋል ብለዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያውያን ወደፊትም አንድነታቸውን አጠናክረው በሀገራቸው ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን በአሸናፊነት መቀልበስ የሚችሉበት ሕያው ማሳያ እንደሆነ ርእሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡
በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ለተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች መላው ኢትዮጵያዊያን ከጎናቸው በመቆም በአዲስ መንፈስ ሕይወታቸውን እንዲጀምሩ ማገዝ እንደሚጠበቅባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ!!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
