‹‹አማራ ክልል በሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ የታዩ ችግሮች በፍጥነት እንዲስተካከሉ ይደረጋል›› ኢንጂነር አይሻ መሐመድ

299

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን ፈጥኖ ለመፍታትና ልማት ላይ ለማዋል የፌዴራልና የክልል የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡ ምልከታ ከተደረገባቸው መካከል የመገጭ ሰራባ መስኖ ልማት ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ጥቅምት 15/2012 ዓ.ም ነበር በወቅቱ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የነበሩት ስለሺ በቀለ (ዶክተር/ኢንጂነር) በተገኙበት የተመረቀው፡፡ በዓለም ባንክ ድጋፍ እና በፌዴራል መንግሥት በጀት የተገነባው ፕሮጀክቱ ከ4 ሺህ በላይ ሄክታር ማሳ ያለማል፡፡ በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ማምረት በማስቻልም ከ30 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ባለበት የዲዛይን፣ የግንባታ እና የአስተዳደር ችግሮች ምክንያት ተገቢውን ጥቅም እየሰጠ አይደለም፡፡ የባለሙያ አለመሟላት፣ የማሽን እቃዎች መለዋወጫ አለመኖርና የኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥ ፕሮጀክቱ ተገቢውን ጥቅም እንዳይሰጥ አድርገውታል፡፡ አንዳንድ ቦታ ቦዮች ኮንክሪት ባለመሆናቸው ውኃ የማስረግ፣ በእንስሳት የመጎዳትና በደለል የመሞላት ችግር ማጋጠሙንም የመስኖ ውኃ ተጠቃሚ ማኅበራት ተወካዮች ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮች ተገቢው ካሳ እንዳልተከፈላቸውም ጠቅሰዋል፡፡ በተፈጠረው ክፍተት ምክንያት ሕዝቡ አመኔታ እያጣ መሆኑን የምሥራቅ እና ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ አስተዳደሮች ተናግረዋል፡፡ የቦይ ሥራዎችና የጥራት ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ምኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በቦታው የተገኙት ለተስተዋሉት ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የሰው ኀይልም ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግ የያነሱት ሚኒስትሯ ፕሮጀክቱ በምን መልኩ መተዳደር እንዳለበትም እየተሠራ ነው ብለዋል።
ሁሉም የድርሻውን እንዲሠራ ለማድረግ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ተግባር ይገባል ብለዋል። የመንግሥት ጥረት ብቻውን ውጤታማ ስለማያደርግ ማሕበረሰቡ በሚችለው አቅም ፕሮጀክቱን እንደራሱ አድርጎ እንዲንከባከብ እና የማስተካከል ኀላፊነት ተጥሎበታል፡፡
የአካባቢው መስተዳድርም ኀላፊነቱን ወስዶ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡ ሀገሪቱ በገጠማት አሁናዊ ችግር ምክንያት የተፈጠረው የካሳ ክፍያ መዘግየትም በሂደት ይፈታል ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ሁመር ሁሴን “የመጣነው ችግር ለመፍታት ነው፤ ከግብርና ጋር ቀጥታ የሚተሳሰሩ ተግባራትን እናስተካክላለን” ብለዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የመገጭ ሰራባ መስኖ ፕሮጀክትን በትንሽ ማስተካከያ በቅርቡ የተዘሩ ሰብሎች እንዳይበላሹ ማድረግ ይቻላል፡፡ 4 ሺህ ሄክታሩ ሙሉ በሙሉ እንዲለማም አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሰጠው አመላክተዋል፡፡
የአካባቢው አርሶ አደሮችም በቦዮች ላይ የሚደርስን ብልሽት እና ልቅ ስምሪትን መከላከል እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በአማራ ክልል የመስኖ ውኃ ፕሮጀክቶች የደረሱበት ደረጃ እና ያለባቸውን ችግሮች እየተገመገመ መኾኑን ያነሱት ደግሞ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪዋ አይናለም ንጉሴ ናቸው፡፡ ችግሮቹን ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር በመተባበር በአጭር ጊዜ ምላሽ እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎቹ ከመገጭ ሰራባ በተጨማሪ የመገጭ እና ርብ የመስኖ ፕሮጀክቶችን የግንባታ ሂደት እና ወቅታዊ አቋም ተመልክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

Previous articleየሽብር ቡድኑ በአማራ እና አፋር ክልሎች በሴቶች እና ህጻናት ላይ የፈጸመውን ጾታዊ ጥቃት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያስገነዝብ ሰልፍ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
Next article“ኢትዮጵያን የምትፈራና የማትደፈር ሀገር ለማድረግ ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል ይገባችኋል” አቶ ላቀ አያሌው