
ታኅሣሥ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በወገን ጦር የተገኘው ድል አስመልክቶ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-
የተገኘው ድል የሚያሳየን የኢትዮጵያን አንድነት ማጽናት በትውልድ ቅብብሎሽ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር የጀግኖቻችን መስዋእትነት ውጤት መሆኑን ነው። የአሁኑ ትውልድም ልክ እንደቀደምት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የገጠመውን ወደር በሌለው ጥላቻና ምቀኝነት ተሞልተው እንዲሁም የታሪካዊ ጠላቶቻችን እቅድ ለማስፈጸም የተነሱ ጎጠኛና ዘረኛ ከትግራይ የተነሳ ቡድንን አሸንፎአል። ድላችን ዘላቂ ለማድረግ ይህን መጥፎ መንፈስ ዳግም ለኢትዮጵያ አንድነት ስጋት በማይሆንበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ትግሉ መቀጠል ይኖርበታል።
የፈጸሙትን ዘግናኝና አረመኔያዊ ወንጀል መረጃውን ሰብስበን፣ አጣርተንና አደራጅተን ትውልዱ እንዲማርበት እናደርጋለን።
የተፈጸመብን ጥቃትና ዘረፋ ከፍተኛ ቢሆንም በመላ ኢትዮጵያውያን ትብብር ወገኖቻችንን መልሰን ማቋቋም እና የወደመውን መልሰን መተካት እንችላለንና ነጻ የወጣችሁ ወገኖቻችን ለቀጣዩ አዲስ የሕይወት ምእራፍ በአዲስ መንፈስ ተነሱ፤ ከተማውን አጽዱ ፤ የአካባቢ ሰላምና ደኅንነታችሁን ጠብቁ፤ የተፈናቀላችሁ ወገኖቻችን ለመመለስ ፈጥናችሁ ተዘጋጁ። መሠረታዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት ለመጀመር መንግሥት ይሠራል። እንደ ጨለመ አይቀርም ነበርና ይሄው መስዋእትነት ተከፍሎ ጨለማው ተገፎአል። ዘላለማዊ ክብርና ምስጋና ለመከላከያ ሠራዊትና ለአማራ ጥምር ኃይል! ምስጋና ለመላ ኢትዮጵያውያን!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
