
ባሕር ዳር፡ መስከረም 24/2012 ዓ/ም (አብመድ) አቶ ምስጋናው አየነው በ1980 ነበር በደጋ ዳሞት ወረዳ በልብስ ስፌት ሥራ የተሰማሩት፡፡ በወቅቱ የልብስ ስፌት ማሽኑን የገዙላቸው አባታቸው ነበሩ፡፡ አቶ ምስጋናው የሚያገኟት ሳንቲም ቁም ነገር እንዳላት በማሰብ ይቆጥቧት ነበር፡፡
‹‹ሥራዬን በአግባቡ እሠራለሁ፣ ጫት አልቅምም፣ ሲጋራ አላጨስም፣ ማንኛውም ደባል ሱስ የለብኝም፡፡ ጊዜዬን በከንቱ ተግባር አላሳልፍም፤ ሁሉም ነገር ሊለወጥ የሚችለው በጊዜ እንደሆነ ስለማምን ለጊዜ ትልቅ ቦታ እሰጣለሁ›› ብለዋል የሕይወት ልምዳቸውን ለአብመድ ሲናገሩ፡፡
አቶ ምስጋናው አየነው ባጠራቀሙት ገንዘብ በ1984 ዓ.ም ሥራቸውን ወደ ጣቃ ልብስ ሽያጭ ማሳደግ ቻሉ፡፡ በዚህ ጊዜም ሥራ ወዳድነታው አብሯቸው ነበርና በደንበጫ ከተማ ወደ ሕንጻ መሣሪያዎች ንግድ ከፍ አደረጉት፡፡
የሥራ ፍቅር እና የጊዜን ፋይዳ ቀድመው የተገነዘቡት አቶ ምስጋናው አየነው፣ ሥራቸውን በተጨማሪ ወደላቀ ደረጃ በማሳደግ ከሌሎች ሰባት የሥራ ባልደርቦቻቸው ጋር በመሆን በደንበጫ ከተማ ‹‹አጌመም ኮንስትራክሽን›› የተባለ የጠጠር ሥራ ድርጅት ለራሳቸውና ለወገናቸው ሕዝብ መትረፍ የሚችል አድርገው መሠረቱ፡፡
ለራሳቸው ብቻ ሀብትን ማካበት ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግዴታቸውንም በሚገባ የተረዱ ናቸው፡፡ ግብር ለሀገር ልማት እንደሚውል ስለሚያውቁ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ ከሚከፍሉ ነጋዴዎች ውስጥ አንዱ መሆን በመቻላቸው በፌዴራል የገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ዛሬ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
በፌዴራል የገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ግብር ከፋይ የሆኑ በሕግ ተገዢነታቸው ለሌሎች አርዓያ የሚሆኑ እና ለቀጣይ ከዚህ የተሻለ ሕግ አክባሪ ሆነው ለሀገራቸው አለኝታ መሆን ለሚችሉ የንግድ ድርጅቶች እና የሥራ ክፍል ሠራተኞች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ በአገር ደረጃ በተካሄደው የዕውቅና ፕሮግራም 10 የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ግብር ከፋዮች ዕውቅና እንዳገኙ እና በዛሬው ቀን 5 ግብር ከፋዮች ዕውቅና እንዳገኙ በኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ደመመ ነግረውናል፤ ከእነዚህ ሰዎች አንዱም አቶ ምስጋናው ናቸው፡፡
እነዚህ ድርጅቶች ዕውቅናን ለማግኘት መረጃዎችን በአግባቡ ያስመዘገቡ፣ የንግድ ዘርፉን በትክክል ለይተው ያስመዘገቡ፣ ትክክለኛ የሆነ እና እየተጠቀሙበት ያለ በድርጅቱ ስም ተመዝግቦ የሚገኝ የሒሳብ ቁጥር ከፋይላቸው ላይ ያስመዘገቡ፣ የ21 ወር ቫት በወቅቱ ያስመዘገቡ እና የከፈሉ፣ የ2009 አና 2010 ዓ.ም የንግድ ትርፍ ያሳወቁና ግብራቸውን በወቅቱ የከፈሉ ለዕውቅናው እንደ መስፈርት መወሰዳቸውን ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡
‹‹ግብርና ታክስ አንድ አገር እንደ አገር እንድትቀጥል ወሳኝ ከሆኑ ሀብቶች የመጀመሪያው ነው›› ያሉት አቶ ካሳሁን ታክስ ከመንግሥት አመሠራረት ጋር ረጅም ታሪክ ያለው እና መንግሥታት የዜጎችን የሠላም፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ እና የፖለቲካዊ ጥቅሞችን ለሟሟላት የሀብት ምንጫቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ አምስት ታታሪ የንግድ ድርጅቶች፣ ሕግ አክባሪ ግብር ከፋዮች እና የቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ ምሥጉን ሠራተኞች ዕውቅና አግኝተዋል፡፡ የዕውቅናው መሰጠት ሌሎች ነጋዴዎች እንደሚማሩበት እና ዕውቅና ያገኙትም የበለጠ ሕግ አክባሪ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ