
ታኅሣሥ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው እና ወራሪው የትግራይ ቡድን በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከሚፈጽመው ግድያ እና ውድመት ጎን ለጎን ሴቶችን መድፈር እና ማንገላታት ዋነኛ ተግባራቶቹ ናቸው፡፡ ይህ እኩይ ምግባር ሳይበግራት በጀግንነት ሲፋለሙ የተጎዱ አምስት የመከላከያ ሠራዊት አባላትን የተንከባከበች ጀግኒት እናስተዋውቃችሁ፡፡
በሰሜን ወሎ መቄት ወረዳ ራስ ደጀን ቀበሌ ነዋሪዋ ሙሉነሽ ዓባይ አሸባሪው ቡድን ወደ ትውልድ ቀየዋ ገብቶ እየፈጸመ ካለው ጥቃት ለመዳን ብዙዎች ህይወታቸውን ለማትረፍ በሚሞክሩበት ጊዜ “ከራሴ ህይወት ይልቅ ደሙን ገብሮ ሀገር ለማቆየት የሚታገለው ወታደር ህይወት ይበልጥብኛል” በሚል በጀግንነት ሲፋለሙ የቆዩና የተጎዱ አምስት የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ተንከባክባ ህይወታቸውን ታድጋለች፡፡ በዚህም የርህራሄ እና የሀገር ወዳድነት ጥግን በተግባር አሳይታለች፡፡
ጉዳዩ እንዲህ ነው ወራሪው እና አሸባሪው የትግራይ ቡድን የከፈተውን ወረራ ለመቀልበስ በግንባር ተሰልፈው ሲዋጉ የቆዩ አምስት ወታደሮች በተጎዱበት ጊዜ ወደ ራስ ደጀን ቀበሌ እንደምንም ይደርሳሉ፡፡ ወቅቱ ምንም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት የቆመበት እና ወታደሮቹን ለህክምና ወደ አቅራቢያ ጤና ተቋም ለመላክ የሚቻልበት አልነበረም፡፡ ወራሪው ቡድን ደግሞ ቀበሌዋን ለመውረር በእውር ድንብር እየተመመ ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ለሀገር ክብር ሲሉ ዋጋ የከፈሉትን ወታደሮች ስታይ ልቧ ያዘነው ሙሉነሽ የአካባቢውን ወጣቶች በማስተባበር በአቅራቢያ ወደሚገኘው ቤተክርስቲያን ወሰደቻቸው፡፡ ወደ ቤቷ ብትወስዳቸው ሊጥ እና ዱቄት ፍለጋ በየቤቱ የሚልከሰከሰው ቡድን ሊያገኛቸው ይችላል በሚል ይህን አላደረገችም፡፡
በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ለፍስለታ ፆም ከተሰበሰበው ምዕመን በደብሩ አለቃ አማካኝነት ገንዘብ በማሰባሰብ ከግል ተቋም መጠነኛ ህክምና እንዲያገኙ አደረገች፡፡ ከዚያም በየቀኑ ከቤቷ እየተመላለሰች ምግብ ደብቃ በመውሰድ፣ ባህላዊ ወጌሻ እና ሐኪም በምስጢር በማፈላለግ አግባብታ እንዲታከሙ ጥረቷን ቀጠለች፡፡
ከቀናት በኋላ አሸባሪው እና ወራሪው የትግራይ ቡድን ቤተክርስቲያኑ የሚገኝበትን አካባቢ ወረረ፤ ሙሉነሽ ጎረቤቷ የሆነውን ወጣት ደጀን ይልማን አስተባብራ በፈረስ አንድ በአንድ በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው አርቢት ወደሚገኝ ሌላ ቤተክርስቲያን አጓጓዘቻቸው፡፡

ደጀን እና ሙሉነሽ ወታደሮቹን በፈረስ ጭነው ወደ ቤተክርስቲያን በሚወስዱበት ጊዜ የአሸባሪው ቡድን አባላት እንዳይዟቸው ዋናውን መስመር ትተው በሚያውቁት አቋራጭ መንገድ መጓዛቸውን ነግረውናል፡፡ ሙሉነሽ በየቀኑ ከቤቷ ወደ ቤተክርስቲያኑ እየተመላለሰች ምግብ እና ውኃ ማቅረቧን ያለማቋረጥ ቀጠለች፡፡
በዚህ ሁኔታ ሦስቱ ወታደሮች ሙሉ ለሙሉ አገግመው በምስጢር ከስፍራው እንዲወጡ አድርጋለች፡፡ እኒህ ወታደሮች አሸባሪውን እና ወራሪውን የትግራይ ቡድን ዳግም በግንባር እየተፋለሙ መሆኑን ሙሉነሽ ነግራናለች፡፡ ከወታደሮቹ ጋር ቤተሰብ ሆነው አሁንም ድረስ እንሚደዋወሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የቀሩት ሁለቱ ወታደሮች ጉዳታቸው ከባድ በመሆኑ በቤተክርስቲያኑ ቆዩ፡፡ የቤተክርስቲያኑ አለቃ ምዕመኑን በማስተባበር ገንዘብም እህልም እንዲያወጡ ያደርጉ ነበር፡፡ ይህም አቅም በፈቀደው ልክ ለተጎጂዎቹ የተሻለ ምግብ እንድታቀርብላቸው ረድቷታል፡፡
ሙሉነሽ የሠራዊቱ አባላትን ደብቃ ለመንከባከብ ያነሳሳትን ምክንያት ስትናገር “ሠራዊቱ ለኔ ክብር እና ደኅንነት ዋጋ እየከፈለ እኔ እነሱን የመርዳት እድል አግኝቼ ባላደርገው የውስጥ ቁስል ስለሚፈጥርብኝ ነው” ነበር ያለችው፡፡
ወጣት ደጀን ይልማም የሙሉነሽን ተግባር ካየ በኋላ የአባቱን ፈረስ እየተዋሰ ታካሚዎቹን ከቦታ ቦታ ሲያመላልስ፣ በቻለው አጋጣሚም ከቤተሰቦቹ ምግብ በመውሰድ ሲንከባከብ መቆየቱን ነግሮናል፡፡ የአሸባሪው እና ወራሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን አባላት ታካሚዎቹን እንዳያገኟቸው ከቤተክርስቲያኖቹ አለቆች ጀምሮ ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉን ነግሮናል፡፡
ለሁለት ወር ከ15 ቀናት በድብቅ እንክብካቤ ሲደረግላቸው የቆዩት ታካሚዎቹ በመጨረሻም በመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ወራሪው ቡድን ድባቅ ተመቶ ከመቄት ወረዳ ሲወጣ መከላከያ ሠራዊትን ተቀላቅለዋል፡፡ ከሁለቱም የሠራዊት አባላት ጋር ቤተሰባዊ ወዳጅነት መመስረታቸውን ሙሉነሽ ገልጻልናለች፡፡
ከታካሚዎቹ መካከል መሠረታዊ ወታደር አበበ አዳነን (ስሙ ለደኅንነት ሲባል የተቀየረ) የአሚኮ የጋዜጠኖች ቡድን በስልክ አነጋግሮታል፡፡ ወታደር አበበ ሙሉነሽ፣ ደጀን እና ሌሎች የመቄት ወረዳ ወጣቶች ለነብሳቸው ሳይሳሱ ህይወታቸውን በመታደጋቸው ምስጋናውን የሚገልጽበት ቃላት እንደሌለው ተናግሯል፡፡ ሙሉነሽንም “ዳግማዊት እቴጌ ጣይቱ” ሲል ገልጿታል፡፡
እቴጌ ጣይቱ በዓድዋ ጦርነት ወቅት የተጎዱትን በመንከባከብ እና ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ ከፍተኛ የሠራዊቱ ደጀን እንደነበሩ ታሪክ ያስታውሰናል፡፡
የሙሉነሽ ዓባይ፣ የደጀን ይልማ እና ሌሎች የመቄት ወረዳ ወጣቶች የኋላ ደጀንነት በግንባር አሸባሪውን እና ወራሪውን የትግራይ ቡድን #ለመደምሰስ እየተዋጋ ለሚገኘው የወገን ጦር ትልቅ ወኔን እና መነቃቃትን እንደሚፈጥር ወታደር አበበ ተናግሯል፡፡
ዘጋቢ:- ቢኒያም መስፍን
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
