“የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ውሳኔ ሰጥቶ ሸንጎ እንደመቀመጥ ነው” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

166

ታኅሣሥ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ትናንት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ልዩ ስብሰባ አድርጎ ነበር፡፡ መንግሥት ስብሰባው ሕጋዊነቱን ያልጠበቀ እና የተወሰኑ አካላትን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት የተደረገ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ ረፋድ ላይ ለብዙኃን መገናኛ ተቋማት መግለጫ የሰጠው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ትናንት ያደረገውን ልዩ ስብሰባ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት ያለመ ነው ሲል ተቃውሞታል፡፡
የተለየ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ኃይሎች ያስተባበሩት ልዩ ስብሰባ ነበር ያሉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ሂደቱንም “ውሳኔ ሰጥቶ ሸንጎ እንደመቀመጥ ነበር” ብለውታል፡፡ ለኢትዮጵያ በጎ እሳቤ የሌላቸው ኃይሎች ቀድመው የወሰኑትን ውሳኔ ለማጽደቅ እንደተሰባሰቡ በመግለጽ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ የልዩ ስብሰባው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን መንግሥት እንደማይቀበል እና እንደማይተባበር ገልጸው ውሳኔው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረጉትን የጋራ ምርመራ የናቀ ነው ብለዋል፡፡
ትልቅ ዓለምአቀፍ ተቋም ለፖለቲካ ፍላጎት መጠቀሚያ መሆኑ ኢትዮጵያን አሳዝኗታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ውሳኔውን የተቃወሙ ሀገራትን መንግሥት ያመሰገናል ነው ያሉት፡፡
የሰብዓዊ መብት አያያዝ ገለልተኛ፣ ሙያዊ መርህን እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባከበረ መንገድ ለማጣራት ለሚፈልግ ዓለም አቀፍ ድርጅት ኢትዮጵያ በሯ ክፍት ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ መንግሥት ለትብብር ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ከሽብር ቡድኑ አባላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ፖሊስ ጠርጥሮ በሕግ ቁጥጥር ሥር ስላዋላቸው ዜጎች ጉዳይም ሚኒስትር ዴኤታዋ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ “ሁላችንም ከሀገር ሉዓላዊነት በታች ነን” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለሀገር ሰላም እና ደኅንነት ስጋት ናቸው በሚል ከተለዩ አካላት ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው ሊጣራ ይችላል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን ከሙያ እና ከፕሬስ ነፃነት ጋር አያይዞ ማየት ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

Previous article❝በኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያን በሚወዱ ኹሉ እገዛ የተጎዱ እና የወደሙ የጤና ተቋሞቻችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሰን እንደምንገነባ አልጠራጠርም❞ ዶክተር ሊያ ታደሰ
Next articleየጀግኒት ደጀንነት በተግባር