
ታኅሣሥ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ላይ የተቃጣውን የኅልውና አደጋ በተባበረ ክንድ እየመከቱት ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው ዘመቻ ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በኹሉም ግንባሮች ተሰልፈው የሚጠበቅባቸውን ኹሉ እያበረከቱ ነው፡፡
በውጭ ሀገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን የተጀመረው “#በቃ” ወይም #NoMore ዘመቻ ደግሞ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው። አፍሪካዊያንና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ዘመቻውን በስፋት እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡
በደቡብ አፍሪካ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባልና የዩናይትድ ሚዲያ ሃውስ መስራች የሆኑት አቶ በኃይሉ መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የኅልውና አደጋ ለመመከት ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ እየሠራ ነው፡፡
በደቡብ አፍሪካና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የውጭ ጣልቃ-ገብነት በሚመለከት ለአፍሪካዊያን የግንዛቤ መፍጠር ተግባር ሲያከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በቅርቡም በደቡብ አፍሪካ የተባበሩት የኢትዮጵያዊያን ማኅበረሰብ ማኅበር ከአፍሪካ ዳያስፖራ ፎረም ጋር በመተባበር ከገንዘብ መዋጮ ጀምሮ ሀገራቸውን ለመደገፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
ከሰሞኑ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት “#በቃ” ዘመቻ አካል የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ በፕሪቶሪያ መካሄዱንም ገልጸዋል፡፡
በሰልፉ “የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካዊያን ይፈታል” የሚለውን እሳቤ በተግባር ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ላደረገላቸው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አፍሪካዊያንን በማሳተፍ ዘመቻው ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሠራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ኅልውና ለማስጠበቅ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በቁርጠኝነት እየሠሩ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
በዚህም በደቡብ አፍሪካና ደቡባዊ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቱ ባሉ ስመ-ጥር መገናኛ ብዙኀን በመቅረብ በሀገራቸው ያለውን እውነት እያሳወቁ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ዳያስፖራው በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት ረገድ የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
