❝ወጣቶች መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀላቸው ታሪክ ለክብር እንዳጫቸው ሊቆጥሩት ይገባል❞ አቶ ክርስቲያን ታደለ

129

ታኅሣሥ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣቶች የሀገር አንድነትና የሕዝብ ኅልውና የመጨረሻ ደጀን ወደ ኾነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት መቀላቀላቸው ታሪክ ለክብር እንዳጫቸው ሊቆጥሩት ይገባል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ጥሪ አቀረቡ፡፡
አቶ ክርስቲያን ታደለ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከውስጥ ባንዳዎችና ከውጭ ኃይሎች ጋር የሞት ሽረት ትግል እያደረገች በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ የልጆቿን አለሁ ባይነት የምትፈልግበት ወቅት ላይ ትገኛለች። ከዚህ አኳያ ወጣቶች የሀገር አንድነትና የሕዝብ ኅልውና የመጨረሻ ደጀን ወደ ኾነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ታሪክ ለክብር እንዳጫቸው ሊቆጥሩት ይገባል ብለዋል።
ውትድርና ጥይት መተኮስ ብቻ ሳይሆን በርካታ የቴክኖሎጂና የምርምር ሙያ መስኮችን አካቶ የያዘ የሙያ ዘርፍ መሆኑን የተናገሩት አቶ ክርስቲያን፤ ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ሲቀላቀሉ ሀገርን የማስጠበቅ የዜግነት ግዴታቸውን ከመወጣት ባለፈ ህልሞቻቸውንም እውን የሚያደርጉበት የተሻለው አማራጭ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል፡፡
ያደጉትም ኾኑ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ታፍረውና ተከብረው የሚኖሩት በመሠረቷቸው ጠንካራ ተቋማት በተለይም በመከላከያ ሠራዊታቸው ነው ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ አባቶቻችን በመስዋእትነት ያስረከቡንን ኢትዮጵያ ወደፊትም ታፍራና ተከብራ እንድትኖር የፀጥታ ኃይሉ የሰለጠነ፣ የተደራጀና ዘመናዊ ሜካናይዝድ የጦር ስልቶችን የተካነ ኾኖ የሀገሩን ህልውና የሚያስጠብቅ ማድረግ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ክርስቲያን ገለጻ፤ እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን ብለን በኩራት እንደምንናገረው ልጆቻችንም በተራቸው የአባቶቻችን ልጆች ነን የሚሉበትን ድል ማስመዝገብ ይጠበቅብናል፡፡ ማንም የውጭ ወራሪ ኃይልና የውስጥ ባንዳዎች ኅልውናዋን የማይፈታተኗት ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ወጣቶች ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት በመቀላቀል የሀገራቸው አለኝታ መሆናቸውን ማስመስከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአደባባይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚከፈለውን ኹሉ እከፍላለሁ እስከ ሲዖልም እወርዳለሁ ብሎ ሲዝት መቆየቱን አስታውሰው፤ ዛቻውን በተግባር ተርጉሞ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለማፍረስ፣ ንጹሐን ዜጎች ላይ ጅምላ ጭፍጨፋዎችን በመፈጸምና ተቋማትን በማፍረስ ሀገረ መንግሥቱ ልፍስፍስና የውጭ ኃይሎች ገባሪና አፋሽ አጎንባሽ እንዲሆን ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ፍላጎቱን ለማሳካትም የሺህ ዓመታት የሥልጣኔ ባለቤት የኾነችውን ኢትዮጵያ ወደ ትናንሽ የመንደር መንግሥታት ለመቀየር እየታተረ ይገኛል ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ አባቶቻችን መስዋእትነት ከፍለው ያስረከቡንን ሀገር መከፈል የሚገባውን ኹሉ ዋጋ በመክፈል አንድነቷና ኅልውናዋ የተረጋገጠ ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ መረባረብ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ እየተደረገ ያለውን የኅልውና ትግል ብዙዎች ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጋር ብቻ የሚደረግ ተጋድሎ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ መኖሩን የተናገሩት አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ ጭንብሉ ሲገፈፍ ግን ትግሉ የሚደረገው በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች ከሚቀኑ፣ ይህን ሀብቷ እንዳትጠቀም ከሚፈልጉና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ከሚያስከብሩ ኃይሎች ጋር ጭምር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የጥፋት ኃይሉና ባለፉት 27 ዓመታት ያዝረከረካቸውን የጥላቻ፣ የመለያየት፣ የመከፋፈል የሐሰት ተረኮች፣ ሕጎችና አሠራሮች ከነሰንኮፉ ተነቅለው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሸኘት ይኖርብናል ብለዋል።
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

Previous articleየሃይማኖት መምህራን እና ዳኢዎች ለተፈናቃይ ወገኖች ከምግብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ ባለፈ የሥነ ልቦና ግንባታ ሥራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቅረበ፡፡
Next article“አፍሪካዊያንን በማሳተፍ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጣልቃገብነት ለማስቆም እየሠራን ነው” በደቡብ አፍሪካ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባልና የዩናይትድ ሚዲያ ሃውስ መስራች አቶ በኃይሉ መሐመድ