“አማራጫችን ማሸነፍ ብቻ ነው” የወገን ጦር አባላት

323

ታኅሣሥ 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “ማሸነፍ ብቻ” የሚለውን ሐሳብ አንግበው የተነሱት የክተት ጥሪ ጀግና ዘማቾች በወሎ ግንባር ጀብድ ሠርተዋል፡፡ ከጀግኖቹ መካከል አቶ አምሳያ አድጎ እንደነገሩን ቃላቸውን ጠብቀው ጠላትን እያርበደበዱ እና አይቀጡ ቅጣት እየቀጡ ጀብድ መሥራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ አቶ አምሳያ በቀያቸው ሆቴል ከፍተው እየሠሩ የተሻለ ኑሮ የነበራቸው ቢሆንም ሠርቶ መኖር፣ ሀብት ማፍራት፣ልጅ ማሳደግ የሚቻለው ሀገር የተረጋጋ እና ሰላም ሲሆን በመሆኑ ቅድሚያ ጠላትን ለመቅበር መወሰናቸውን ነው ያብራሩት፡፡
በወሎ ግንባር በመገኘት ከወገን ጦር ጋር በመቀናጀት በፈጸሙት ታላቅ ጀብድም ጠላትን በማንበርከክ በርካታ አካባቢዎችን ነፃ ማውጣት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ በተሰለፉባቸው አውደ ውጊያዎች ሁሉ ጠላት ከፊት የሚቆምበት ሞራል እንዳልነበረው እና የያዘውን መሳሪያ ትቶ አስክሬን እንኳን ሳያነሳ መፈርጠጡን አይተዋል፡፡ ጀግኖች ከጥምር ጦሩ ጋር በመሆን የፈጸሙት ጀብድ በታሪክ ከፍ ብሎ የሚዘከር እንደሆነም አቶ አምሳያ ነግረውናል።
ሌላኛው ጀግና የወሎ ግንባር ዘማች ጥላሁን ዳኛው እንደገለጹት ጠላትን ደምስሰው እንዲመለሱ ሕዝብ መርቆ እንደሸኛቸውና የሕዝብን አደራ ጠብቀው ጠላትን ቀጥተው ጀብድ ፈጽመዋል፡፡ ጀግኖቹ ሕዝቡ የሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት ከወገን ጦር ጋር በመኾን እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ በርካታ አካባቢዎች ነፃ እንዲወጡ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በተለይም የከላላ ወረዳን፣ ለጋምቦን፣ አቀስታን፣ ገነቴ እና ሌሎች አካባቢዎችን ነፃ በማውጣት ነዋሪዎች የሰላም አየር እንዲተነፍሱ ማስቻላቸውን ነው በኩራት የገለጹት፡፡
በቀጣይም በተገኘው ድል ሳይኩራሩ ወራሪ ቡድኑን እስከ መጨረሻው #ለማጥፋት በቁርጠኝነት እንደሚታገሉ ዘማች ጥላሁን አረጋግጠዋል፡፡
ሕዝቡ ሀገር እንዲጠብቅና እንዲያስከብር ለላከው ጀግና ስንቅ በማቅረብ፣ ሰብል በመሰብሰብ እና በመንከባከብ ያሳየው ደጀንነት ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ዘማቹ ሐሳቡን ወደ ቤተሰብ ሳያደርግ ሙሉ ትኩረቱን አውደ ውግያው ላይ እንዲያደርግ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡ “ያለን አማራጭ ጠላትን ማሸነፍ ብቻ ነው፤ ስለሆነም የሕዝቡ ደጀንነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ነው ያሉት
የዘመቻው አስተባባሪ ዓለሙ ሰውነት እጅግ ቆፍጣና፣ የማሸነፍ ሥነልቦና እና ወኔ የተላበሰ ዘማችን መምራት እንደሚያስደስት አስረድተዋል፡፡ ዘማቾች ጠላትን ከወገን ጋር ተናበው ጀብድ በመሥራት መቅጣታቸውን ነው የገለጹት፡፡
ከወገን ጦር ጋር በመሆን ባካሄዱት ፍልሚያ ጠላት በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎችን ማስለቀቅ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ ጠላት የያዘውን ቦታ እንዲለቅ ብቻም ሳይኾን እንደ ቅጠል ረግፎ ሙት፣ ቁስለኛ እና ምርኮኛ እንዲኾን ማድረግ መቻላቸውንም ተናግረዋል።
ደጀን የኾነው ሕዝብ ራሱን በማደራጀት አካባቢውን ሊጠብቅ ይገባል፤ ወጣቶችም መከላከያ ሠራዊትን እና ልዩ ኀይልን በመቀላቀል ሀገራቸውን ሊጠብቁና ሊያስከብሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፦አዳሙ ሽባባው-ከወሎ ግንባር
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

Previous articleኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሚተላለፉ ውሳኔዎች እንደማትቀበል አስታወቀች።
Next articleየሃይማኖት መምህራን እና ዳኢዎች ለተፈናቃይ ወገኖች ከምግብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ ባለፈ የሥነ ልቦና ግንባታ ሥራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቅረበ፡፡