ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሚተላለፉ ውሳኔዎች እንደማትቀበል አስታወቀች።

171

ታኅሣሥ 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሚተላለፉ የትኛውም አይነት ውሳኔዎች እንደማትቀበልና እንደማትተገብር አስታወቀች።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ዙሪያ የጠራው ልዩ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።
በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረጉትን የጋራ ምርመራ የናቀ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለቱ ተቋማት የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝና የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ ኃይልም ተቋቁሞ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህ ባለበት ሁኔታ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የጋራ ጥናቱን ወደ ጎን በመተው ይሄን ስብሰባ እንዲጠራ ማድረጉ የተወሰኑ ኃይሎች የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ልዩ ስብሰባው የጋራ ጥናቱን በመናቅ የጠራው ኢትዮጵያን የማተራመስ አጀንዳ ያለውና ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ የሚተላለፉ የትኛውም አይነት ውሳኔዎች እንደማትቀበል፣ እንደማትተገብርና ትብብር እንደማታደርግ ነው አምባሳደር ዘነበ ያስገነዘቡት።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት በስብሰባው ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ እንዲቃወሙና ውድቅ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ምክር ቤቱ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ንጹሐንን በመጨፍጨፍ፣ ሴቶችን በመድፈር፣ የጤናና የትምህርት ተቋማትንና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ዘረፋና ውድመት ሲፈጽም አለማውገዙና ዝምታን መምረጡ የምክር ቤቱን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ ምርመራ ለማድረግ ፍላጎት አለማሳየቱና የፖለቲካ ጫና ለማሳደር እንደ መሳሪያነት መዋሉ የሚያሳዝን መሆኑን ነው አምባሳደር ዘነበ ያስረዱት።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን በመጀመሪያው የጋራ ሪፖርታቸው ያልዳሰሷቸውን የአማራና አፋር ክልሎች ላይ ምርምራ እንዲያደርግ ጥሪ ታቀርባለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና እንዲጠበቁ በቁርጠኝነት እንደምትሠራ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ሊጭኑባት የፈለጉ ኃይሎችን ብቻዋን በዓለም መድረክ በመታገል አሸንፋለች አሁንም ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ትግሏን ትቀጥላለች ብለዋል።
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

Previous articleኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ከመጓዝ የሚያግዳት አንድም ኀይል እንደማይኖር የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ተናገሩ፡፡
Next article“አማራጫችን ማሸነፍ ብቻ ነው” የወገን ጦር አባላት