
ባሕር ዳር፡ መስከረም 24/2012 ዓ/ም (አብመድ) የአማራ ክልል መንግሥት የአማራና ቅማንት ሕዝቦች በሠላም በፍቅር እና በአንድነት እንዲኖሩ ዕድል ፈጥሮ እያለ ሰሞኑን በአዲስ መልክ የሕዝቦችን ሠላም እና አንድነት የማይፈልጉ አካላት “የቅማንት ማንነት እና የራስ አስተዳድር ጥያቄ አልተመለሰም” በሚል የፖለቲካ አሻጥር ሠላማዊ ዜጎችን እርስ በርስ በማጋጨት በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የቅማንት ብሔረሰብ ያነሳውን የማንነት እና የራስ አስተዳድር ጥያቄ የመለሰበት አግባብ ዴሞክራሲያዊና ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን በሚችል መልኩ እንደሆነ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ አዳሙ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
“‘የቅማንት የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄ አልተመለሰም’ የሚሉ አካላት ትክክል አይድሉም ጥያቄዉ እንደተመለሰላቸዉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተቀብሎ አጽድቋል፤ ‘ሌሎች ተጨማሪ ሦስት ቀበሌዎች ወደ ቅማንት ይካለሉ’ የሚሉ ጥያቄዎችም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርበዋል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የጥናት ቡድን ልኮ ቀበሌዎቹ ኩታ-ገጠም አለመሆናቸዉን አረጋግጧል፤ ስለዚህ ጥያቄያቸው ተገቢ አይደለም ተብሏል” ነው ያሉት አቶ ወርቁ፡፡
የክልሉ መንግሥት ዋናዉን ጥያቄ በቀላሉ መመለስ የቻለ በመሆኑ አሁንም እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን ሕጋዊ አግባብነታቸዉን አይቶና አጥንቶ መፍታት ሲቻል ግጭት እንዲፈጠር መደረጉ ተገቢ አለመሆኑንም ነው አቶ ወርቁ የተናገሩት፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህሩ ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴም “የአማራ ክልል ከሕገ መንግሥቱ መጽደቅም አስቀድሞ በ1986 ዓ.ም ለብሔረሰብ አስተዳደሮች ዕውቅና መስጠት የጀመረ፤ የዋግ ኽምራ፣ አዊና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደሮች እንዲመሠረቱ ያደረገ፤ በኋላም የአርጎባ ልዩ ወረዳን ዕውቅና የሰጠ፤ የቅማትንም ጥያቄ ተቀብሎ ለተግባራዊ ምላሽ እየሠራ የሚገኝና ለሌሎችም ምሣሌ የሚሆን ነው” ብለዋል::
የቅማንት ብሔረሰብን የማንነት እና የራስ አስተዳድር ጥያቄን ለመመለስ የአማራ ክልል ምክር ቤት በ2010 ዓ.ም አዲስ ልዩ አስተዳድር ሆኖ እንዲደራጅ በመወሰን ወደ አፈጸጸም ለመግባት ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ይህን የክልሉን ውሳኔ ለመቀበልና ወደ ተግባር ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆኑ የኮሚቴ አባላት መኖራቸውን ተከትሎ አካባቢው በተደጋጋሚ ለፀጥታ መደፍረስ እየተጋለጠ እንደሆነ ነዋሪዎች እና መንግሥት ይገልጻሉ፡፡
ከሰሞኑም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከማንነት ጋር በተያያዘ ሰበብ የፀጥታ መደፍረስ አጋጥሞ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረትም ወድሟል፡፡
ከቀናት በፊት ጀምሮ ደግሞ አካባቢው ወደ ሠላማዊ እንቅስቃሴ መመለስ እንደጀመረ መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ -ከአዲስ አበባ