ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ከመጓዝ የሚያግዳት አንድም ኀይል እንደማይኖር የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ተናገሩ፡፡

128

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በሴቶች እና በሕጻናት ላይ ያደረሰውን ኢ-ሰብዓዊ ጥቃትና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ሰልፍ በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተካሂዷል፡፡
የሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፉ ዋንኛ ዓላማ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በሴቶች እና በሕፃናት ላይ ያደረሰውን ኢ-ሰብዓዊ ጥቃት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅ፣ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ እያደረጉ ያሉትን ጣልቃገብነት መቃወም እና የኢትዮጵያን ሐቅ ማሰማት ነው፡፡ ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ወንጀለኞች በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲጠየቁ እና የሽብር ቡድኑን እድሜ ለማራዘም የሚንቀሳቀሱ ሀገራት እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱም ልዩ ልዩ መልዕክቶችን ሰልፈኞቹ አሰምተዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እንሠራለን የሚሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ችግሩን ማስቆም ሲገባቸው ለሽብር ቡድኑ የሚያደርጉት ድጋፍ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ አሸባሪው የትግይ ወራሪ ቡድን በፈጸመው የግፍ ወረራ በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞች እና በአረጋውያን ላይ አስከፊ እና ጭካኔ የተሞላበት ኢሰብዓዊ ጥቃት መፈጸምን እንደ አንድ የጦር ስልት ተጠቅሞበታል ብለዋል፡፡ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቆመናል ያሉ አካላት ይህንን ድርጊት ለማውገዝ ቸልተኝነታቸው እና ፍርደ ገምድልነታቸውን ያሳዩበት መሆኑ ደግሞ ጥቃቱን ድርብ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡ ሆኖም የወገን ጦር ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ ያሳየው ጀግንነት እና የኢትዮጵያውያን አንድነት ያመጣው ውጤት በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ እንዲኖር አድርጎል ብለዋል፡፡
አፈ ጉባዔዋ እንዳሉት በሴቶች ላይ የደረሰውን አስከፊ ጥቃት ማውገዝ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ሀገሪቱ በጠንካራ መሠረት ላይ እንድትጸና ማድረግም ከሕዝቦቿ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም አቅም ያለው ሁሉ መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል፣ እናቶችም ልጆቻቸውን መርቀው መላክ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም ከተጎዱት ጎን ቆመው ፍትሕን ለማረጋገጥ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ‹‹ኢትዮጵያ ዛሬም ጠላቶቿን አሸንፋ በክብር ከፍ ብላለች፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በእብሪት የተነሳው ወንበዴ፣ ተላላኪዎቹ እና አጋሮቹ ደግሞ ተሸንፈዋል›› ብለዋል።
ጠላት ሀገሪቱን የማፍረስ ሕልም ካላቸው አካላት ጋር የቻለውን ኹሉ ቢያደርግም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ከመጓዝ የሚያግዳት አንድም ኀይል አይኖርም ነው ያሉት። ፈተናዎችን ተጋፍጠው ሀገሪቱ የገጠማትን ፈተና ለመቀልበስ ብርቱ ትግል ያደረጉ ሴቶችም ታሪክ የማይረሳው አኩሪ ገድል እየፈጸሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢንጂነር አይሻ እንዳሉት ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ እና የሕዝቦቿን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ትግል ማቀጣጠል አሁንም ከኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ አስናቁ ድረስ እንደገለጹት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በእብሪት እና በማናለብኝነት በፈጸመው ወረራ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ እናቶች የጤና አገልግሎት አጥተው በዱር በገደሉ ወልደዋል፤ ከሕፃናት እስከ መነኩሴ በቡድን ተደፍረው ለጤና እና ለሥነልቦና ጉዳት ተጋልጠዋል። ብዙዎች በርሃብ አለንጋ ተገርፈዋል፡፡ መንግሥት ጦርነቱን ለማጠናቀቅ በሚያደርገው ትግል አኩሪ ድል እየተገኘ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸውን የመንከባከብ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ነገር ግን የረድኤት ድርጅቶች ለተጎዱ ወገኖች እያደረጉ ያለው ድጋፍ አናሳ መሆኑን ነው ወይዘሮ አስናቁ የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleበሽብር ቡድኑ ወረራ የታጣውን ምርት በመስኖ ልማት ለማካካስ እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሚተላለፉ ውሳኔዎች እንደማትቀበል አስታወቀች።