በሽብር ቡድኑ ወረራ የታጣውን ምርት በመስኖ ልማት ለማካካስ እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

110

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወረራቸው የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶችን አድርሷል፡፡
አሸባሪው ቡድን በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ ከሁለት ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት ሰብል አውድሟል፤ ከ42 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት አሳጥቷል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አምሳሉ ጎባው እንደተናገሩት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወረራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ካወደመው ሰብል በተጨማሪ የአርሶ አደር ማሠልጠኛ ጣቢያዎችን፣ የግብርና ባለሙያዎች ማሠልጠኛ ተቋማትን፣ የግብርና የምርምር ተቋማትን እንዲሁም በአይነቱ ልዩ የሆነውን የደሴ ቲሹ ካልቸር የምርምር ተቋምን ጨምሮ ሌሎች ግብርናውን የሚደግፉ ተቋማትን ዘርፏል፤ አውድሟል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ የችግሩን መጠን ለማወቅ ባደረገው የመጀመሪያ የዳሰሳ ጥናት ከ42 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት አሳጥቷል፤ ይህንን ሊያካክስ የሚችል እቅድ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡ ለሀገር ኢኮኖሚ መሠረት የሆነውን የግብርና ዘርፍ ከችግር ለማውጣት መረባረብ ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው እንዳሉት በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ባልተወረሩ አካባቢዎች ከ80 ሽህ ሄክታር በላይ መሬት በአንደኛ ዙር መስኖ በስንዴ ዘር በመሸፈን ከ4 ሚሊዬን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለሥራው ውጤታማነት የሥራ ኀላፊዎች እና የግብርና ባለሙያው በቅንጅት ይሠራሉ፤ ለምርምር እና ለድጋፉ ዩኒቨርሲቲዎች እና የግብርና ምርምር ተቋማት ይሳተፋሉ፤ በገንዘብ ለመደገፍ ባለሃብቶች ተሠልፈዋል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ ያለውን ሀብት በማቀናጀት የባከነውን ምርት ለማካካስ እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ውኃ ገብ መሬቶች በመስኖ እንዲለሙ እየተደረገ መሆኑን አቶ አምሳሉ ተናግረዋል፡፡ የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳይከሰት ለማድረግ ከፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር እና ከጎረቤት ክልሎች ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አቶ አምሳሉ “እኛ እያለን ወገኖቻችን የእርዳታ ስንዴ አይጠብቁም በማለት ትልልቅ ባለሀብቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና አርሶ አደሮች የገቡትን ቃል በተግባር ለመፈጸም እየተረባረቡ ይገኛሉ” ነው ያሉት፡፡
ለመስኖ የሚውሉ ታላላቅ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ለልማት የሚውሉበት መንገድ መመቻቸቱን የጠቀሱት ኀላፊው በዚህ ዓመት ያለሥራ የሚከርም መሬት፣ ውኃ፣ ሞተር እና ጉልበት አይኖርም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!

Previous articleበ’አንድ ሚሊዮን ወደ የሀገር ቤት’ ጥሪ የጤና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ዘመቻ ተጀመረ።
Next articleኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ከመጓዝ የሚያግዳት አንድም ኀይል እንደማይኖር የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ተናገሩ፡፡