
‹‹አዴፓ ለማንም አቤቱታ ማቅረብ ሳይሆን መንግሥት በመሆኑ ሕግን ተንተርሶ ሕግ እንዲከበር ማድረግ ይኖርበታል›› አዴኃን
ባሕር ዳር፡ መስከረም 24/2012 ዓ/ም (አብመድ) ከሰሞኑ በማዕከላዊ ጎንደር የተፈጠረው ግጭት የተለያዩ ጥፋቶችን አድርሷል፡፡ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረትም ወድሟል፡፡ የተፈጸመው ድርጊት ሆን ተብሎ የአማራን ሕዝብ ለማዳከም እና የክልሉ ሕዝብ ሠላም እንዳይኖረው ለማድረግ የተቀነባበረ ሴራ መሆኑን የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀ መንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ ተናግረዋል፡፡
‹‹የተፈጸመው እኩይ ተግባር ከክልሉ አልፎ ሀገሪቱን ስጋት ላይ የሚጥል በመሆኑ የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ከተሰለፉ አካላት ጋር ድርጊቱን ለመከላከል በጋራ እንሠራለን›› ያሉት አቶ ተስሁን በተፈጠረው ችግር ዙሪያ የክልሉ መንግሥት የያዘው አቋም የንቅናቄውም አቋም እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
እንደ አቶ ተስፋሁን ማብራሪያ የአማራን ሕዝብ በኢኮኖሚ ለማዳከም እና ሠላም ለመንሳት የተቀናበረ ሴራ ነው፤ ይህ ደግሞ በአንድም በሌላም መንገድ የአማራን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱንም የሚጎዳ ነው፤ አካባቢው ከሌሎች ሀገሮች ጋር አዋሳኝ በመሆኑ ቀጠናው ሠላም ማጣቱ ክልሉን ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ይጎዳል፡፡ ‹‹ፀረ ሠላም ኃይሎቹ ልዩነት የሌላቸውን ሕዝቦች ልዩነት እንዳላቸው በማስመሰል ለመነጣጠል ሽፋን እየሰጡ የውክልና ጦርነት እያካሄዱ ነው›› ያሉት አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ አዴፓ የያዘው አቋም ትክክል በመሆኑ የፓርቲያቸው አቋምም መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
‹‹አዴፓ ለእርምጃ ዘግይቷል›› ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን የተናገሩት የአዴኃን ሊቀመንበር አሁንም ቢሆን ክልሉን እረፍት ለመንሳት ፀረ ሠላም ኃይሎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመመከት ከአዴፓ ጋርም ሆነ ከሌሎች የክልሉ ጉዳይ ይመለከተኛል ከሚሉ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡
ግጭቱ በሕዝቦች መካከል የተፈጠረ ሳይሆን የቅማንት ብሔረሰብን ሽፋን በማድረግ ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግሥ በሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች አማካኝነት የተፈጠረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መልካሙ ሹምየ ናቸው፡፡ ድርጊቱ የአማራ ክልልን ሕዝቦች አንድነት እና አብሮነትን ለመሸርሸር የተፈጸመ በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ አንድነቱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ሕዝቡ ብልህ እና አስተዋይ በመሆኑ አብዛኛውን ግጭት እያከሸፈ መምጣቱን የተናገሩት አቶ መልካሙ ሹምየ ‹‹ይህ እሴት እንዲሁ የመጣ ሳይሆን ለሺህ ዓመታት ያካበተው እና አብሮት የመጣ ነው፤ ሕዝቡ ለሺህ ዓመታት ክፉውንም ደጉንም አብሮ የተሻገረ ነው፤ ይህ ጊዜያዊ ችግር ነው፤ የአማራን ሕዝብ ያለውን አንድነት ለማናጋት፤ በሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እንዲጠላ በማድረግ በሁሉም አቅጣጫ ጥቃት እንዲፈጸምበት በማድረግ ለማዳከም እና ለማጥፋት የሚፈልግ አካል የሚደግፈው መሆኑን ሕዝቡ ስለሚረዳም ነው ወደ ተደገሰለት የእልቂት ጉድጓድ ባለመግባት ተልኮውን እያከሸፈ የመጣው›› ብለዋል፡፡
‹‹አሁንም በተለመደው አስተውሎት የአማራን ሕዝብ ለጥፋት የሚፈልጉ ኃይሎችን በአንድነት፣ ክፍተት ሳይፈጥር፣ የፖለቲካ እና የግጭት ነጋዴዎችን ተልኮ ማክሸፍ አለበት›› ብለዋል አቶ መልካሙ ሹምየ፡፡
የክልሉ መንግሥት መሰል እኩይ ተግባራት እንዳይፈጸሙ አስቀድሞ በዘላቂነት የመከላከል ሥራውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሊሠራ እንደሚገባው ያሳሰቡት አቶ መልካሙ ‹‹ጉዳዩ ቀደም ብሎ ሲከሰት የነበረ ነው፤ በመሆኑም በዘላቂነት መፈታት አለበት፤ ችግር ሲፈጠር ብቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ከመሯሯጥ ቅድመ ዝግጅት መደረግ አለበት›› ብለዋል፡፡
አሁን ያለው ችግር በአንጻራዊነትም ቢሆን ወደ ሠላም የመጣው የደም ዋጋ ተከፍሎበት መሆኑን ያስታወሱት አቶ መልካሙ የደም ዋጋ ከመከፈሉ በፊት የክልሉ መንግሥት አስቀድሞ መረጃዎችን በመሰብሰብ መከላከል እንዳለበትና እነዚህ ኃይሎች ችግር እንደሚፈጥሩ መረጃው ያለው መንግሥት ማወቁ ብቻ መፍትሔ ስለማይሆን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የቅድመ መከላከል ሥራ መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
‹‹በግጭት አስተዳደር ላይ መጀመሪያ ግጭትን መከላከል ይቀድማል፤ በተለይ ሲደጋገም ልምድ ወስዶ በአስተማማኝ ሁኔታ መከላከል ያስፈልጋል፤ ከመከላከል