
አዲስ አበባ፡ ታኅሣሥ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኝነቱን ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ የጠራዉን ስብሰባ መንግሥት በጽኑ እንደሚቃወም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ገልጸዋል፡፡ ስብሰባው ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ ሀገራትን የመደገፍ እሳቤ መሆኑንም ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ያካሄደውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ የሌሎች የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ሆኖ ይገኛል ብለዋል። የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል ብቻ ከ 2ሺህ 813 በላይ የጤና ተቋማትን ቢያወድምም የዓለም አቀፉ የጤና ተቋም ዝምታ መምረጡ የአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት የፖለቲካ ማስፈጸሚያ መሆኑን ያሳያልም ነው ያሉት።
ዩኔስኮም አሸባሪ ቡድኑ በቅርስ ላይ እያደረሰዉ ያለዉን ጉዳት በዝምታ አልፎታል ነው ያሉት።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ድርጊትን አፍሪካዉያን እንዲቃወሙም መንግሥት ጥሪ አስተላልፏል ብለዋል። የተቋሙ ድርጊት የአፍሪካውያን አባል ሀገራትን ፍላጎት ከግምት ያላስገባ እንደሆነም አስረድተዋል።
አዲስ አበባ በአሳሳቢ ሁኔታ ትገኛለች የሚለዉ የአሜሪካ ኤምባሲ የሐሰት መረጃም መሰረተ ቢስ መሆኑ የታየበት ወቅት እንደሆነም ነው የጠቆሙት።
ኢትዮጵያውያንም ወደ ሀገራቸዉ የሚመጡ እንግዶቻቸውን ለመቀበል ዝግጁ ኾነው እየጠበቁ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉኡሽ-ከአዲስ አበባ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!! 
            
		