
ታኅሣሥ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኩራት የሆነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከጀርባው ወግቶ የለኮሰው ጦርነት ራሱን መልሶ እየለበለበው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀውን ክህደት የፈጸመው አሸባሪው ቡድን በሥልጣን ዘመኑ በፈጸማቸው ከባድ ወንጀሎች በሕግ እንዳይጠየቅ ሀገር የማፍረስ ዓላማን ሰንቆ በሕዝባዊ ማዕበል የትግራይን ሕዝብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ወደ ጦርነት ማግዶ የእሳት እራት አድርጎታል፡፡
መንግሥት በተደጋጋሚ ተጨባጭ ማስረጃዎችን በማስደገፍ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ሕፃናትን እያስታጠቀ እና ወታደራዊ ሥልጠና እየሠጠ ወደ ጦርነት እየማገደ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ይህ እውነታ አይሰማውም፡፡
በሚገባ ከታጠቀ እና ዘመናዊ ከሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በሀገሩ ቀልድ ከማያውቀው ኢትዮጵያዊ ጋር አጉል ግብግብ የገጠመው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የኔ የሚለውን ሕዝብ ከየቤቱ መዝመት አለባችሁ እያለ በየ ጦር ግንባሩ አስጨርሶ የሰው ኀይል እጥረት ገጥሞታል፡፡
ይህንን ክፍተት ለመሙላት በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ሕፃናትን ወደ ጦርነት እያሠማራ መሆኑን በጠለምት ወረዳ ከሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ አምልጦ የመጣው የ13 ዓመት ሕፃን አይቶልኝ ሰገድ ተናግሯል፡፡
ሕፃን አይቶልኝ ሰገድ ዓይነ ስውር እናቱን እየመራ የሚኖር የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ የአሸባሪ ቡድኑ አባላት ሕፃን አይቶልኝን ከዓይነ ስውር እናቱ ነጥቀው ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ አስገቡት፡፡ እንደ ሕፃኑ ምስክርነት ከሱ ጋር በርካታ ሕፃናት በወታደራዊ ማሰልጠኛው ገብተዋል፡፡ መትረየስ፣ ክላሽ መፈታታት እና መገጣጠምም ተምሯል፤ መተኮስም እንደሚችል ነግሮናል፡፡ በማሰልጠኛው ሕፃናት ጦርነቱን እንዲለማመዱ ዲሽቃ፣ ብሬን እና ክላሽ በትከሻቸው ላይ እየተደረገ ይተኮስ እንደነበር ተናግሯል፡፡
የሚደነግጥ እና የሚያለቅስ ሕፃን የከፋ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ ሕፃናቱ ከባድ ድብደባ እና እንግልት ሲደርስባቸው መመልከቱንም ተናግሯል፡፡ በወታደራዊ ማሰልጠኛው ሕፃናት ወላጆቻቸውን እየናፈቁ እና የሚደርስባቸውን በደል መቋቋም እየተሳናቸው ሲያለቅሱ እና ለከፋ ስቃይ እየተዳረጉ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን አባላት ርህራሔ የሚባል ያልፈጠረባቸው አረመኔዎች መሆናቸውን ሕፃን አይቶልኝ እንባ በዐይኑ እያቀረረ ነው የሚገልጸው፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪው ያለውን ገንዘብ፣ ጌጣ ጌጥ፣ ያለውን እቃ እና እህል ማዋጣት ግድ ይለዋል፡፡ ይህ የተዋጣ ሃብት በቀጥታ ለወራሪ ቡድኑ የጦርነት እንቅስቃሴ እየዋለ ነው፡፡ አሸባሪ ቡድኑ በተለይ ሕፃናትን ፆታ ሳይለይ ከቤተሰቦቻቸው እየነጠቀ በቀጥታ በጦርነቱ ያሳትፋል፤ ለስለላ ያሰማራል፤ የወሲብ ባሪያ አድርጎ እያሰቃያቸው እንደሆነ ምርኮኛ ሕፃናቱ ይናገራሉ፡፡
መንግሥት እና ሕዝቡ የጀመሩትን አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን የማጥፋት ዘመቻ በፍጥነት ጨርሰው በተለይ ሕፃናቱ ከአረመኔ ቡድኑ ነፃ እንዲወጡ ሕፃን አይቶልኝ የአደራ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ዘጋቢ፡-የማነብርሃን ጌታቸው
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
