
ደሴ፡ ታኅሣሥ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና መሰል ተቋማት በጦርነት ወቅት ጥበቃ እንደሚደረግላቸው የዓለም አቀፍ ሕጎች ይደነግጋሉ። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ግን የዓለም አቀፍ ሕጎችን በሚፃረር መልኩ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ሁሉ በሰብዓዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ እጅግ ከባድ ውድመትና ዘረፋ ፈጽሟል።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ባደረገባቸው የደቡብ ወሎ ዞኖች ግዙፉን የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የደሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ፣ የኮምቦልቻ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ፣ የወይዘሮ ስህን ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ፣ የሁጤ አጠቃላይ መሰናዶ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ቤት እና ሌሎችንም የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ አውድሞ እና ዘርፎ መሄዱን የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
ያነጋገርናቸው የተቋሙ ኀላፊዎችም የደረሰው ዝርፊያ እና ውድመት “ወራሪው ቡድን የፈጸመው ድርጊት በታሪክ የማይረሳና ቡድኑ የሕዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር ያስመሰከረበት ነው” ብለዋል።
የሁጤ አጠቃላይ መሰናዶ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት ርዕሰ መምህር መኩዮ ካሳው እንደገለፁት በደሴ ከተማ የሚገኘው የሁጤ አጠቃላይ መሰናዶ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1961 የተመሰረተ እና የክልሉ አንጋፋ ከሚባሉት ተቋማት አንዱ ነው። ትምህርት ቤቱ 170 መምህራን እና 31 የአስተዳደር ሠራተኞችን በመያዝ ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ የሚገኝ ነበር ብለዋል። ከ53 ዓመት በላይ ትውልድን የቀረፀው እና አንጋፋው የሁጤ አጠቃላይ መሰናዶ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በወራሪው ቡድን ተዘርፏል፣ የፊዚክስ እና ኬሚስትሪ የተማሪዎች ሠርቶ ማሳያ ክፍሎች፣ 82 የፕላዝማ የትምህርት መስጫ ቁሳቁስ እና ኮምፒውተሮች መቃጠላቸውን ርዕስ መምህሩ ተናግረዋል።

እንደ ርዕስ መምህሩ ገለፃ ትምህርት ቤቱ ከ21 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ውድመት እና ዝርፊያ ደርሶበታል። ውድመት እና ዝርፊያውም ተማሪዎች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ታቅዶበት የተሠራ ነው፤ ትምህርት ቤቱም ለጠላት እጅ መስጠት ስለሌለበት ጠመኔ እና ጥቁር ሰሌዳ ይዞ ሥራውን ያስቀጥላል ብለዋል። ያም ሆኖ ግን የክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ የቀድሞ ተማሪዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እገዛ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ሌላኛው ከፍተኛ ውድመት እና ዝርፊያ የደረሰበት ተቋም የደሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ነው። የኮሌጁ ምክትል ዲን ወይዘሮ አልማዝ ብርሃኑ እንደገለጹት በ1972 የተመሠረተው ኮሌጅ ከ50 ሺህ በላይ መምህራንን በማፍራት ትውልድን በመቅረጽ ከፍተኛ አበርክቶ አለው። በአሁኑ ወቅትም ከ200 በላይ ምህራንና 1ሺህ 700 ተማሪዎች ያሉት ነው። በቀጣይ ዓመትም ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በማደግ የዲግሪ ፕሮግራም ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ ነበር ነው ያሉት። ይህ ኮሌጅ ግን በወራሪው ቡድን ከፍተኛ ዘረፋ እና ውድመት ደርሶበታል ብለዋል። ወራሪ ቡድኑ በተለየ መልኩ በትምህርት ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት እና ዝርፊያም ተተኪ ትውልድ ለመጉዳት ዓላማ ተደርጎበት የተፈጸመ ድርጊት ስለመሆኑ አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ወንዶሶን አቢ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የፈጸመው ዝርፊያ እና ውድመት አማራን በጠላትነት ፈርጆ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አንግቦ የተነሳበትን እቅድ በተግባር ያሳየበት ነው ብለዋል።
በደሴ እና አካባቢዎቹ በቆየባቸው ጊዜያት የፈጸማቸው ድርጊቶችም እውነተኛ የአማራ ጠላት መሆኑን ያሳየበት እንደሆነ ተናግረዋል። ወራሪ ቡድኑ የነገ ትውልድ መገንቢያ የሆኑትን የትምህርት ተቋማት አውድሟል፤ ይህም የአማራን የነገን ሕይወት ለማበላሸት የፈጸመው ተግባር ነው ብለዋል።
“ዘረፋ እና ውድመት በደረሰባቸው አካባቢዎች የመማር ማስተማር ሥራን በፍጥነት በማስጀመር የጠላት ዓላማ እንዳይሳካ እናደርጋለን” ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ለተግባራዊነቱም ግብረ ኀይል ተቋቁሞ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በምዕራብ ወሎ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተያዘው ሳምንት የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንደጀመሩም ጠቁመዋል።
ጠላት ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ መምህራን እና ተማሪዎችም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጣል፤ ተማሪዎች ትምህርት ቤት መዋል ስላለባቸው ትምህርት በአስቸኳይ ይጀምራል ነው ያሉት አቶ ወንዶሰን።
ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ መምህራን እና አጠቃላይ የትምህርት ባለሙያዎች እና የሥራ ኀላፊዎችም ለአንድ ዓመት ትምህርት ማቆም ማለት የጠላትን ግብ ማሳካት መሆኑን በመገንዘብ በቁጭት ሊነሱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች መቋረጥ የሌለባቸውን ሥራዎችን እያስቀጠሉ የሽብር ቡድኑ ዳግም እንዳያንሠራራ አምርረው መፋለም እንዳለባቸው ምክትል ቢሮ ኀላፊው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦አዳሙ ሽባባው-ከደሴ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
