ʺሀገርህን ጠላት እንዳይደፍራት፣ ወታደር ሆነህ ጠብቃት”

889

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን ታሪክ ከማውራት የዘለለ ተግባር ይጠብቅሃል፣ ታሪክ መሥራት አለብህና፡፡ በትናንት ታላቅ ታሪክህ ኩራበት፣ በዛሬ እድልህ ታሪክ ሥራበት፣ ከብረህ ተከበርበት፣ ነገ ላይ የማይጠፋ ስም አስቀምጥበት፣ አንተ በአባቶችህ ታሪክ እንደ ኮራህ ሁሉ ልጆችህም በአንተ ታሪክ ይኮሩ ዘንድ ታሪክ ሥራ፡፡ ኢትዮጵያዊያን አባቶችና እናቶች ወድቆ የማይሰበር፣ ሞቶ የማይቀበር ታላቅ ስም አስቀምጠው፣ በወርቅ ብዕር በማያረጅ ብራና ላይ ታሪክ ጽፈው አልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የሚኮሩባቸው፣ ዓለም የተደመመባቸው፣ ጥቁር ነጻ የወጣባቸው፣ የብርሃን ዘመን የታየባቸው፣ የነጭ አብዮት የተገረሰሰባቸው፣ ፍትሕ የመጣባቸው፣ የአፍሪቃ ምድር ከትብታብ የወጣችበት፣ የነጩ ዓለም የደነገጠበት፣ ጥቁር ኃያል ሆኖ የወጣበት ያዘ ዘመን፣ ያ የድል ቀን፣ ያ ጀብዱ የተጻፈው በደም ቀለም ነው፡፡ ሞትን የናቁ ኢትዮጵያውያን ባይዘምቱ፣ ጠላትን ባይመቱ ኖሮ ያዘ ዘመን ባልመጣ ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን ተዋርዶ ከመኖር ሞቶ መከበርን ይመርጣሉ፤ ለዚያም ነው ነጭ ለብሰው፣ በፈረስ ገስግሰው፣ በጎራዴ የጠላትን አንገት ቀንጥሰው ደማቅ ታሪክ የጻፉት፣ የመከራውን ዘመን በጀግንነት ታሪክ ሰርተው ያለፉት፡፡ የጀግንነታቸው ልክ ከቅጠል ጋር የሚመሳሰል ልብስ እንኳን አለበሱም ነበር፣ በአሻገር የሚታይ ነጭ ለብሰው፣ ጎራዴ ስለው ገቡ እንጂ፡፡ እነርሱ አይፈሩምና፡፡
የኢትዮጵያ አርበኞች ሞት አይፈሩም፣ ሀገር ተነክታ ከቤታቸው አያድሩም፣ በሀገር ጉዳይ አይደራደሩም፣ ጣላት ወሰን ሲሻገር፣ ወገን ሲደፈር ተቆጥተው፣ ስንቃቸውን አዘጋጅተው፣ ጎራዴያቸውን አስተካክለው ይገሰግሳሉ፣ የመጣውን ጠላት በመጣበት መንገድ ቀጥተው ይመልሳሉ፡፡ ለሀገር የሚሰስቱት ሕይዎት፣ ሀብት ብሎ ነገር የለም፡፡

አሸናፊነት መሠረቷ በሆነች ሀገር መወለድ እድለኛነት ነው፡፡ ብዙዎች ኢትዮጵያዊ ባለመሆናቸው ይቀናሉ፣ ኢትዮጵያን ይናፍቃሉ፣ በምድሯ ይኖሩ ዘንድ ይመኛሉ፣ እርሷ ከተለዩት የተለዬች፣ ከተመረጡት የተመረጠች፣ በአሸናፊነት የፀናች፣ ለድል ብቻ የተፈጠረች ሀገር ናትና፡፡ ለኢትዮጵያ ከማሸነፍ በስተቀር ሌላው አይስማማትም፡፡ ማሸነፍ ብቻ በሚስማማት ሀገር መወለድ ደግሞ ኩራት ነው፡፡
ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና እንድትኖር፣ በወዳጆችም በጠላቶችም ዘንድ እንድትከበር፣ ምድሯ እንዳይደፈር ደም ፈስሶላታል፣ አጥንት ተከስክሶላታል፣ ሕይወት ተገብሮላታል፡፡ ጀግንነት የእናት አባት ውርስ፣ የክብር ልብስ፣ የሕይወት ጌጥ፣ ከዘመን ዘመን የማይለወጥ፣ ከደም ስር ጋር የተሳሰረ፣ ከኢትዮጵያውያን ጋር የኖረ ነውና በየዘመናቱ በምድሯ ጀግኖች አይጠፉም፣ በኢትዮጵያ ምድር ጀግና እንደ ምንጭ ውኃ ይፈልቃል፣ ሳያቋርጥ እንደ ጅረት ይፈስሳል፣ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ጀግናም ይተካካል፣ የአባቱን ጋሻ ልጁ እያነሳ፣ የአባቱን ታሪክ ልጁ እያወሳ፣ በጀግንት ይፋለማል፣ የጀግና ሥራ ይሠራል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር እልፍ ጀግኖች ተወልደውባታል፣ እልፍ ጠላቶችም ተነስተውባታል፡፡ በአሸናፊነት ብቻ የጸናው ታሪካቸው የቆጫቸው፣ አልበገርም ባይነቷ ያበሳጫቸው ጠላቶች ነፍጥ እያነሱ፣ ሠራዊት እያዘመቱ ብዙ ጊዜ ሞክረዋታል፡፡ ዳሩ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ይጠናቀቃል እንጂ፡፡
ኢትዮጵያውያን ብቻ የሚያውቁት፣ የኢትዮጵያ ፍቅር ያላቸው ብቻ የሚረዱት፣ ጠላቶች ያልተረዱት ያልገባቸው፣ ምስጢሩ ያልተገለጠላቸው የኢትዮጵያውያን ውድ ምስጢር አለ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ይሉት መንፈስ፣ በጠላት የማይገረሰስ፣ በመከራ ዘመን የማይፈርስ፣ በጠላቶች እጅ የማይረክስ፣ ይልቁንስ የጠላትን የግፍ ተራራ የሚገረስስ፣ የግፍ ሰንሰለት የሚበጣጥስ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ኃያል ነው የማይረታ፣ ኢትዮጵያዊነት ውሉ ጥብቅ ነው የማይፈታ፣ ኢትዮጵያዊነት እሳት ነው የሚያቃጥል፣ ኢትዮጵያዊነት አስፈሪ ግርማ ነው ጠላትን የሚጥል፣ ይህን ነው ጠላቶች የማያውቁት፣ መርምረው ያልደረሱበት፣ መላ ያጡለት፡፡
ኢትዮጵያ እንድትከበር፣ በምንም በማንም እንዳትደፈር አያሌ ጀግኖች ዘብ ቆመውላታል፣ በደማቸው ስሟን አስጠርተውላታል፣ በጀግንነታቸው ዝናዋ በዓለም እንዲናኝ አድርገዋታል፣ የኢትዮጵያ አያሌ ታሪኮች የተሠሩት፣ ወሰኖቿ የተከበሩት በጦረኞች፣ በአርበኞች ነው፣ ጥቁር ነጻ የወጣበት፣ የኢትዮጵያ ስም ከፍ ብሎ የተጠራበት፣ አፍሪቃ የጨለማውን ካባ አውልቃ የጣለችበት፣ ጥቁር የሆነ ሁሉ መመኪያ ያገኘበት፣ ተስፋ ያጡ ተስፋ ያገኙበት፣ ነጻ ያልወጡት ነጻ መውጫውን መንገድ ያዩበት ዓድዋ የተገኘው በአርበኞች፣ በጀግኖች፣ በጦረኞች ነው፡፡ ከዓድዋ በፊትም ሆነ በኋላ በኢትዮጵያ አያሌ ታሪኮች በአርበኞች፣ በጀግኖች፣ በጦረኞች ተሰርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ጉዳይ ሁሉም አርበኛ፣ ሁሉም ጦረኛ ነው፡፡ ሁሉም ሠንደቁን አስቀድሞ ይገሰግሳል፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ ጀብዱ እየሠሩ ዛሬ ላይ ኮርተን የምንኖርባት ሀገር፣ ኮርተን የምንናገረው፣ በአሸናፊነት የምንመሰክረው ታሪክ አኑረውልናል፣ እኒያ ጀግኖች ታሪክ ሰርተው፣ ስማቸውን ከመቃብር በላይ ትተው
ʺሀገሩን ያስደፈረ ታሪክ ይውቀሰው፣ አጽማችንም ይውጋው” ብለው ቃል ኪዳን አስረው፣ አደራ ሰጥተው አልፈዋል፡፡ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን የአባት አደራ አለባቸው፤ ያልተደፈረች ሀገር ተቀብለዋልና፤ በታሪክ ከመኩራት ያለፈ ታሪክ መሥራት ግድ ብሏል፡፡ ዛሬ ታሪክ መስራት ካልቻልክ፣ ዛሬ ለሀገርህ ዘብ ካልቆምክ፣ ዛሬ ሠንደቋን ካላከበርክ፣ ድንበሯን ካላስከበርክ፣ አለሁልሽ ካላልክ የቀደሙትን ጀግኖች አደራ መብላት ይሆናል፡፡
ʺአደራ ከሰማይ ይርቃል ” እንዲሉ አበው አደራን መጠበቅ፣ ኢትዮጵያን ማክበርና ማስከበር ግድ ይላል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ የአንተ ናት፡፡ እንድትጠብቃት፣ እንድታከብራት፣ እንድታስከብራት፣ ታሪኳን እንድታስቀጥልላት የተሰጠችህ፡፡
አባቶች ከእነክብሯ ያስረከቡህ፣ አደራ የሰጡህ፣ በክብር የተሰጠኀትን ውብ ሀገር በክብር ለማስረከብ ታዲያ ተነስና ጠብቃት፣ ዘብሽ ነኝ በላት፡፡
ሀገርህን ጠላት እንዳይደፍራት፣ ወታደር ሆነህ ጠብቃት፣ እንደ አባቶችህ ጀግና ሆነህ አሳያት፣ በጀግንነት ታሪክ ሥራላት፣ ታሪክ ያለው ከወታደርነት ነው፣ ጀግንነት ያለው ከወታደርነት ነው፣ ጀብዱ ያለው ከወታደርነት ነው፣ ታላቅ ስም ያለው ከወታደርነት ነው፣ ዓድዋ የአርበኝነት፣ የወታደርነት ውጤት ነው፣ የአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራና የኢትዮጵያዊያን ድል የወታደርነት ውጤት ነው፡፡ ካራማራ የወታደርነት ውጤት ነው፣ የኢትዮጵያ የተከበረ ታሪክ የወታደር ታሪክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተከበረችው በወታደሮች ክንድ ነው፡፡ ልብ በል ሌሎች ታሪኮችንም እንዳትዘነጋ፡፡
የከበረ ታሪክ እንዲኖርህ፣ ዓለም እንዲያደንቅህ፣ ትውልድ እንዲያከብርህ፣ ጠላት እንዲፈራህ ከፈለክ ወታደር ሁን፡፡ ለኢትዮጵያ ወታደር ኾኖ ኢትዮጵያን ከመጠበቅ የዘለለ ክብር የለም፣ ለኢትዮጵያዊ ክብሩ ኢትዮጵያን መጠበቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የክብር ሁሉ መጨረሻ፣ የውጊያ ሁሉ ድል መንሻ ናትና፡፡ ኢትዮጵያ እየጠራችህ፣ ና ጠብቀኝ እያለችህ ዝም ካልክ የኢትዮጵያዊ ደም በውስጥህ የለም ማለት ነው፡፡ ልብ በል የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ለሀገራችን እንዝመትላት፣ ለሀገራችን እንውደቅላት እያሉ እየለመኑ ይሄዱ እንደነበር አስብ፡፡ የእነዚያ ልጆች ከሆንክ፣ የኢትዮጵያዊ ደም በውስጥህ ካለ ተነስ ሳትውል ሳታድር ኢትዮጵያን አስከበር፡፡
ደማቅ ታሪክ ለመጻፍ የምትሻ ከሆነ ዛሬውኑ ወታደር ሁን፣ ኢትዮጵያን ከወደድካት ዋሷና ጠበቃዋ ሁንላት፣ ወታደር ሆነህ ዝመትላት፣ ታጥቀህ በድንበሯ ኑርላት፡፡ ወታደር ስትሆን ነው ትውልድ የሚኮራብህ፣ ታሪክ የሚያከብርህ፣ ስምህ በወርቅ ቀለም የሚጻፍልህ፡፡ ስምህ በማይጠፋ የወርቅ ቀለም፣ በማያረጅ ብርና ይጻፍ ዘንድ ዛሬውኑ ተነስና ለኢትዮጵያ ወታደር ሁንላት!
በታርቆ ክንዴ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleአንድ ሚሊዬን ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙ ተገለጸ፡፡
Next article‹‹የሐይቅ ሆስፒታል በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጥ አስፈላጊውን እገዛ እናደርጋለን›› የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ያሬድ አግደዉ