አንድ ሚሊዬን ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙ ተገለጸ፡፡

255

አዲስ አበባ፡ ታኅሣሥ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን ውጭ ከሁሉም ጎረቤት ሀገራት መሪዎች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል። ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ማለትም ከሴኔጋል እና ከደቡብ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር ተወያይተዋል ብለዋል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ሕብረት ምክርቤት ፕሬዝዳንት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ እና ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል። ከሁሉም ሀገራት እና የተቋማት መሪዎች ጋር የተደረገው ወይይት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ዙሪያ መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ገዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሳምንቱ ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመሰል ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውንም አምባሳደር ዲና አስረድተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞች በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የምግብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አምባሳደር ዲና በሰጡት መግለጫቸው አብራርተዋል። ሰራተኞቹ ከድጋፉ ባለፈ የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር በሚያስችል ሁኔታ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደሚንቀሳቀሱም ተነግሯል።
እንደ አምባሳደር ዲና መግለጫ በኢትዮጵያ የዲያስፖራ እንቅስቃሴ ታሪክ የመጀመሪያው እንደሆነ የተነገረለት ‟የበቃ“ እንቅስቃሴ በዚህ ሳምንትም ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለሀገራቸው በመቆም የሚያደርጉት ሰልፍ በሳምንቱም ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ አንስተዋል።
በልደት በዓል ሰሞን አንድ ሚሊዬን ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚመራው ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleየዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ወጣቶች መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ሀገራቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገለጹ።
Next articleʺሀገርህን ጠላት እንዳይደፍራት፣ ወታደር ሆነህ ጠብቃት”