
ታኅሣሥ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ወታደርነት ከራስ በፊት ለሀገርና ለሕዝብ መኖር ነው። ውትድርና ሳይንስም ጥበብም ነው። ወታደርነት ታላቅ ግብረ ገብነት የሚቀሰምበት ትምሕርት ቤት ነው።
ለራስ ክብር ብሎም ለወገን የኩራት ምንጭ ለመሆን መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል ወቅቱ የሚጠይቀው ኃላፊነት ነው። ይህንን ታላቅ ተቋም በመቀላቀል ጊዜው የሚጠይቀውን ኃላፊነት እንወጣለን ያሉ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ወጣቶች እየተመዘገቡ ነው።
ተቋሙን ለመቀላቀል ሲመዘገብ አሚኮ ያገኘው ወጣት ዳንኤል ወርቁ ለሙያው ፍቅር እንዳለው ገልጿል። ተቋሙን ተቀላቅሎ ሀገሩን ከጠላት ከመከላከል ባለፈ ወታደራዊ ሳይንስ ለማጥናት ፍላጎት እንዳለው ነግሮናል።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን እየፈጸመ ያለው ግድያ፣ ማፈናቀል እና የንብረት ውድመት በፈጠረበት ቁጭት በዋግ ግንባር እየተደረገ ባለው ተጋድሎ በሎጀስቲክስ አቅርቦት እና በተለያዩ ሥራዎች መሳተፉን ያነሳው ወጣቱ አሁን ላይ ደግሞ መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ለሀገሩ ዘብ ለመሆን መወሰኑን ነው የተናገረው። ሌሎች ወጣቶችም ተቋሙን በመቀላቀል በሀገሪቱ ላይ የተቃጣውን ውስጣዊ እና ውጫዊ አደጋ የመመከት ታሪካዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
ወጣት ግርማይ ፈጠነም የውጭ እና የውስጥ ጠላትን በመፋለም የሀገራቸውን ነጻነት ያስከበሩ ጀግኖችን ገድል ለመድገም የሀገር መከላከያ ተቋምን ተቀላቅሏል።
የታፈረች እና የተከበረች ሀገር እንድትኖረን ከተፈለገ ሀገር ተረካቢ የሆነው ወጣት ተቋሙን በመቀላቀል ሀገሩን ማገልገል ይገባልም ብሏል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ ተስፋየ ገብሬ እንዳሉት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ወጣቶች ወደ መከላከያ እንዲቀላቀሉ እየተሠራ ይገኛል፤ ተቋሙንም በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ። ዋግ ኽምራ ራሳቸውን ሰውተው የሀገራቸውን ነጻነት ያጎናጸፉ፣ በዚህ ወቅትም ለሀገራቸው እየተዋደቁ የሚገኙ ታላላቅ ጀግኖችን ያፈለቀ መኾኑን አንስተዋል።
በኅልውና ዘመቻውም ወጣቶች አካባቢያቸውን ላለማስደፈር ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ያነሱት አስተዳዳሪው ይህንን ጀግንነታቸውን የሀገር መከላከያ ተቋምን በመቀላቀል እንዲያስቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
