ʺአንድ ሁለት እያለ እያለሳለሰ፣ የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢቱ ደረሰ”

856

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የናቋት ወደቁ፣ የደፈሯት አለቁ፣ እርሷን ነክቶ የኖረ፣ እርሷን አዋርዶ የተከበረ አልተገኘም። አበው ʺማስጠንቀቂያም አታደርገኝ፣ ማስጠንቀቂያም አትንሳኝ” ይላሉ። የክፉ ነገር ማስተማሪያ እንዳይሆኑ ሲማፀኑ። እነሆ የናቋት ሀገር ቀጣቻቸው፣ የደፈሩት ሕዝብ መታቸው፣ እናዋርድህ ያሉት ሕዝብ አዋረዳቸው፣ በዘመናት ቅብብሎች የከዱት፣ ያስከዱት፣ ጠላት ሆነው የተነሱበት፣ ጠላት ጎትተው ያስገቡበት፣ ያስመቱት፣ የመቱት ሕዝብ በገቡበት ሁሉ አስቀራቸው፣ በክንዱ ደቆሳቸው፣ ማንነቱን አሳያቸው፡፡
በጀግንነቱ ስለሚበልጣቸው፣ በአርቆ አሳቢነቱ ክፉ ሕልማቸውን፣ ቁንጽል አመለካከታቸውን በእንጩጩው ስለሚቀጭባቸው አብዝተው ይጠሉታል፡፡ ከጠላት ጋር አብረው ይወጉታል፣ መጥለፊያ ወጥመድ ያዘጋጁሉታል፡፡ እርሱ ግን የተጠመደበትን ወጥመድ እየበጣጠሰ፣ የክፋታቸውን ተራራ እየናደ፣ የመደበቂያቸውን ዋሻ እያፈራረሰ በቆፈሩት ይቀብራቸዋል፣ ባጠመዱት ይይዛቸዋል፣ በገመዳቸው እያሰረ ያንቃቸዋል፡፡
ጀግና ሕዝብ ነው ከከፍታው የማይወርድ፣ ቃሉን ጠባቂ ነው ሠንደቅና ሀገር ከሕይወቱ በላይ የሚወድ፣ ፍትሕ አዋቂ ነው ቀኝ ግራውን አይቶ በሚዛን የሚፈርድ፣ ኩሩ ነው የሰው ገንዘብ የማይነካ፣ ማንቱን የማያስነካ፣ በደሙ ጠብታ ሀገሩን ያጸናታል፣ በአጥንቱ ብርታት ይገነባታል፣ ሕይወቱን ሰጥቶ ያቆማታል፣ ኢትዮጵያን ከነኩበት ሕይወት፣ ምቾት ብሎ ነገር አያስብም፣ ዳሯን ሊያስከብር፣ የጠላቷን እግር ሊሰብር ጠላት መጣበት ወደተባለበት ሁሉ ይገሰግሳል፡፡ ተድላና ደስታ በሀገር ላይ ነውና፡፡
በየዘመናቱ በኢትዮጵያ ላይ የተነሱ ጠላቶች ሁሉ ክንዱን ቀምሰዋል፣ ተመትተው አፈር ለብሰዋል፡፡ የአባቶቻቸውን ምኞት ልጆቻቸው እየተቀበሉ፣ በዱር በገደሉ እየተማማሉ ኢትዮጵያን ሊደፍሩ ደጋግመው ሞክረዋል፣ ዳሩ አንዳቸውም አልተሳካላቸውም፣ ሁሉም እንደ አባቶቻቸው ሞተዋል፣ አፈር ኾነዋል፤ ጠላቶች መክረው ዘክረው ቢመለሱም ከጀግንነቱ የማይጎድለው ጀግና ሕዝብ በጀግንነት ይጠብቃቸዋል፣ እንደ አመጣጣቸው ይመልሳቸዋል፣ በእግር መጡ ጨረሳቸው፣ እርሱ ጎራዴና የቃታ ብረት ይዞ በሰማይ ሞከሩ አንጥሮ ተኩሶ ጣላቸው፣ ጀግንነቱ ከሀሳባቸው፣ ከትጥቃቸው፣ ከአቅማቸው ከሁሉም በላይ ሆነባቸው፡፡
በጦር ሲያቅታቸው፣ በሰማይም በምድርም ሲጥላቸው፣ ለወሬ ነጋሪ ሳይተው ሲጨርሳቸው፣ ከወገኖቹ ሊነጥሉት፣ ብቻውን ነጥለው ሊያጠቁት ሌላ ዘዴ ዘየዱ፡፡ ጨቋኝ ነው ሲሉ የውሸት ትርክት ሠሩለት፣ በየፈርጁ የሠራውን አስደማሚ ታሪክ ደበቁበት፣ በወርቅ ቀለም የተጻፈውን ደማቅ ታሪኩን ከመዝገብ ላይ ሊፍቁት፣ በጨለማ ውስጥ ሊደብቁት ፈለጉ፣ ታሪኩን አጥፍተው ሊያጠፉት አማራቸው፡፡ እርሱ ግን ጀግንነቴ የኖሩኩበት፣ ከእናትና አባት የተቀበልኩት፣ ከደሜ ጋር ያዋሃድኩት፣ ተወልጄ ያደኩበት ነውና አትችሉኝም አላቸው፤ እንደ አመጣጣቸው አቀመሳቸው፣ ጀግናው አማራ፡፡
አማራ አትንኩኝ ይላል እንጂ አይነካም፣ አማራ አትንኩኝ ሲል ተነክቷል፣ ሆ ብሎ ተነስቷል፣ ነፍጡን አንስቷል፣ ለሀገሩና ለራሱ የገባውን ቃል እየፈጸመ ነው፡፡ ʺያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ” በሚለው ጠንካራ ቢሁሉ ያለውን ሊያጸና ዘምቷል፣ ነፍጡን አንስቷል፡፡ አማራ ላያደርግ አይናገርም፣ ላይጨርስ አይጀምርም፡፡ አስቀድሞ እንደነገራቸው እየመታቸው፣ እየደመሰሳቸው ነው፡፡
ከዓመታት በፊት የተነገረው ትንቢት እየተፈፀመ ይመስላል። አበው የሚናገሩትን፣ አብዝተውም የሚያምኑትን አትንካባቸው፣ ሲሆን የትንቢት መፈፀሚያ አታድርገኝ፣ በቁጣህ አትቅጣኝ በል። ያ ካልሆነ ግን ትንቢት ይፈፀምብሃል። ትውልድ ይስቅብሃል፣ ታሪክም ይታዘብሃል፣ አሁን እየሆነ ያለው ይሄው ነው፡፡ አበው ያከበሩት፣ በልባቸው አትመው ይዘውት የኖሩት፣ እንደሚፈጸም የጠበቁት እየሆነ ነው፡፡ ብልሁ ሼሕ የተነበዩት፣ አስቀድመው የተናገሩት እየደረሰ ይመስላል፡፡ የጠላት መቀበሪያ ትሆናች ያሏት ምድር እየሆነች ነው፡፡
በጥላቻ ሰክሮ ከትግራይ ዋሻዎች የተነሳው አሸባሪና ወራሪ ቡድን በጀግኖች ክንድ እየደቀቀ፣ ከቀን ወደ ቀን እያለቀ ሄዷል፡፡ ጨርሶ የመጥፊያው ዘመንም የደረሰ ይመስላል፡፡ የማይነካውን ነክቷልና እሳቱ እየፈጀው ነው፡፡ ረመጡ እያቃጠለው ነው፡፡ አፈሙዝ እየበላው፣ ጥይት እየቆላው፣ የጀግኖች በትር እያንዘረዘረው መውጫ ጠፍቶበታል፡፡ አይደለም ቤተ መንግሥት የወጣባቸው የተንቤን ዋሻዎች ናፍቀውት ይቀራሉ፡፡ በአውታር ተወጥሯልና መውጫና ማምለጫ ጠፍቶበታል፡፡
ʺአንድ ሁለት እያለ እያለሳለሰ፣
የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢቱ ደረሰ ” የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንብት አንድ ሁለት እያለ እየደረሰ ነው፡፡ እየገቡ እየቀሩ፣ እየመጡ እያለቁ ነውና፡፡ ጀግኖች የጀግንነታቸውን ውጤት እያገኙ ነው፣ ጠላቶችም የዘሩትን እያጨዱ ነው፡፡ ክፉ አድርጎ ማን ያልፍና፣ ማንስ በሰላም ይኖርና፡፡ የተገፋው ላይቀመጥ ተነስቷል፡፡ ላይበርድ ቁጣው ፈልቷል፡፡ ቁጣው የሚበርደው ድል አድርጎ ጠላት ሲጠፋ ብቻ ነው፡፡
ጀግኖች የዋሉባቸው ሸንተረሮች፣ ሸለቆዎች ሜዳዎች ጠላትን አላላውስ፣ አላንቀሳቅስ ብለዋል፡፡ እነርሱ የሚዋጉት ሀገር ከሚሸጥ ጋር ሳይሆን ለሀገር ደሙን ከሚሰጥ ጋር ነውና፡፡ ስንዝር የማያላውሱት እኒያ ወርቃማ ስፍራዎች ጠላትን እንደ ጀግና ጦረኛ እየያዙ እያቆሙት፣ ለወገን እያስረከቡት ነው፡፡ ጠላትም እጅ ወደ ላይ እያለ ሰግዶ እየተማረከ፣ ቀበቶ ፈትቶ እየተንበረከከ ነው፡፡
አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ ይዞ የሚገሰግሰው ጀግና ሠራዊት ድል በደል እየሆነ ነው፣ አሸናፊነት ከእርሱ ጋር ብቻ ናት፡፡ ሠንደቁን ይዞ ወጥቶ፣ ኢትዮጵያን ብሎ ተነስቶ ያፈረ የለምና፡፡ አሁን የሚጠሏት ፈርተዋል፣ የሚነኳት ደንግጠዋል፣ የደፈሯት ተንኮታኩተዋል፡፡ የተነኩት፣ የተገፉት፣ ተበዳይ ሆነው ሳለ እንደበደለኛ የተቆጠሩት፣ ፍትሕ አዋቂዎች ሆነው ሳለ ፍትሕ የተነፈጉት፣ እንኑር ባሉ የተወቀሱት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተነስተዋል፡፡ እንብኝ አሻፈረኝ፣ በቃን አትነካኩን ብለዋል፡፡ በክንዳችን እንኖራለን፣ በአንድነታችን እንከበራለን እያሉ ነው፡፡
ኢትዮዮጵያውያን በቃ ካሉ፣ በሠንደቁ ግርጌ ከተማማሉ፣ በአንድነት ከተመሙ፣ ቁጣቸው ይጋረፋል፣ ሞገዳቸው ይጋፋል፣ ሕብረታቸው ጠላትን ያጠፋል፡፡ የኢትዮጵያዊነት እሳት በዓለም ላይ ተለኩሷል፣ የኢትዮጵያዊነት ማዕበል ገንፍሏል፣ እሳቱም ያቃጥላል፣ ማዕበሉም ይውጣል፤
አዎ አንተም ለፍትሕ፣ ለነጻነት፣ ለአንድነት፣ ለኢትዮጵያዊነት፣ ለሰብዓዊነት በቃ በል፡፡ በቃ ብለህ ተነስ በክፋት የተዘረጉትን እጆች መልስ፣ በቃ በል እንብኝ በል፣ እንብኝ ስትል ነው የምትፈራ፣ እምብኝ ስትል ነው አኩሪ ታሪክ የምትሠራ፣ እምብኝ ስትል ነው ጠላት የሚርድ፣ እምብኝ ስትል ነው ለአንተ የሚሰግድ፡፡ ወዳጄ ቁጣህ ሳይበርድ እንደጋለ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ሥራ፡፡ ጠላትህን አጥፍተህ፣ ለጠላት የማይደፈር ሕዝብና ሀገር ገንብተህ ቀን ጠብቀው መነሳት ላሰቡት አሳያቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ቀዬን ማርከስ አይደረግም በላቸው፡፡ ክንድህን አፈርጥምባቸው፣ የጀግንነትክን ጥላ ጣልባቸው፣ ያን ጊዜ ለዘላላም ያከብሩሃል፡፡
እምብኝ ብለህ መነሳትህ ለቀናት፣ ለወራት፣ ወይንም ለጥቂት ዓመታት ብቻ እንዳይሆኑ የማይነቃነቅ አንድነት፣ የማይደፈር ጉልበት ፈጥረህ እምብኝ ማለትህን ለዘመናት አድርገው እንጂ፡፡ እነዚያ ቀን ጠብቀው የሚነሱትን ጠላቶችህን ታሳቢ አድርገህ ተነስ፣ በአንድነት ገስግስ፡፡ እንዲያ ያደረክ እንደሆነ በየዘመናቱ ከአሸናፊነት ላይ አሸናፊነት እየጨመርክ በአማረ ጎዳና በኩራት ትጓዛለህ፡፡ ከነፍስህ አስበልጠህ የምትወዳትን ኢትዮጵያንም ከወገኖችህ ጋር ታላቅ የማትደፈር ሀገር ታደርጋለህ፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

Previous articleበወራሪው የጠላት ኃይል ላይ መንግሥት እየወሰደ ካለው የተጠናከረ የማጥቃት እርምጃ ጎን ለጎን በሀገሪቱ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቋቋም እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።
Next articleየዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ወጣቶች መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ሀገራቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገለጹ።