
ታኅሣሥ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ እና መልሶ ማቋቋም ተልዕኮ ዙሪያ ለመንግሥት አስፈፃሚ አካላት የሥራ ስምሪት የሰጠበት መድረክ አካሄዷል።
የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ በአሁን ጊዜ መንግሥት በወራሪ የጠላት ኃይል ላይ እየወሰደ የሚገኘው የማጥቃት እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በወራሪ ጠላት ላይ ከሚወሰደው የማጥቃት እርምጃ ጎን ለጎን በሀገሪቱ የሚደርሱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለመቋቋም እና ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ኹለንተናዊ ጥረት በቅንጅት ለመምራት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁንም አቶ ደመቀ ይፋ አድርገዋል።
እንደ አቶ ደመቀ ገለጻ በጠላት ወረራ ተይዘው የተለቀቁ፤ በጠላት በተወረሩ አካባቢዎች እንዲሁም በአርብቶ አደሩ አካባቢ የደረሰውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም የሚያስችሉ ኹሉአቀፍ ድጋፎች በልዩ ትኩረት ይከናወናሉ።
“በዚህ ረገድ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የዕለት ደራሽ ዕርዳታ አቅርቦት፣ የማገገም እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን አስመልክቶ በተጠና እና በሰመረ ቅንጅት ኃላፊነታቸውን በጋራ ሊወጡ ይገባል” ብለዋል።
በሀገሪቱ ለተከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በሚሰጡ ምላሾችና የመልሶ ማቋቋም ተግባራት ዙሪያ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት በጋራ ሊረባረቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት በጠላት ላይ በሚደረገው መጠነሰፊ የማጥቃት ዘመቻን ተከትሎ የሚለቀቁ አካባቢዎችን መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመር የሚያስችሉ ድጋፎችን በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ፤ እያንዳንዱ ሴክተር ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ መጠበቅ እንደሚገባ አስምረውበታል።
በመድረኩ ኢትዮጵያ ካላት መልክዓምድራዊ አቀማመጥ እና የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሁኔታዎች በተያያዘ ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጋላጭ እንደሆነች አቶ ደመቀ አብራርተዋል። በመሆኑም በገጠር አርሶ አደሩ ፈጥኖ ወደ በጋ የግብርና ሥራ እንዲገባ የመስኖ ልማት ባለባቸው አካባቢዎች የተለያዩ አስፈላጊ የእርሻ ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
በተለያየ አግባብ በተደራጁ የድጋፍ ሰጪ እና የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴዎች በተመለከተ በመካከላቸው ያለውን የሥራ ድግግሞሽ በማስቀረት ተጠያቂነትንና ኃላፊነትን በሚያረጋግጥ መንገድ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ብለዋል አቶ ደመቀ።
የብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ እና መልሶ ማቋቋም ተልዕኮ ዙሪያ ለመንግሥት አስፈፃሚ አካላት የሥራ ስምሪት መስጠቱን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
