
ደሴ፡ ታኅሣሥ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ደሴ ቅርንጫፍ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት መድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎችን መዘረፉንና ማውደሙን ኤጀንሲው አስታውቋል።
በአማራ ክልል ከሚገኙ ሦስት ግዙፍ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲዎች መካከል አንዱ ነው፤ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ደሴ ቅርንጫፍ። ቅርንጫፉ እጅግ ዘመናዊ እንደነበርም የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን አረጋግጧል።
በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ደሴ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ እሸቴ ሹሜ እንደገለጹት የደሴ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በምሥራቅ አማራ ለሚገኙ 60 ወረዳዎች፣ 29 ሆስፒታሎች፣ 308 ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም ከ45 በላይ የግል ጤና ተቋማት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ነው። እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ ይህ ግዙፍ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲው ሙሉ በሙሉ ተዘርፏል፤ ወድሟል። ከ70 በላይ በሲስተም የተያያዘ ኮምፒውተሮችም በሙሉ ተወስደዋል።
በኤጀንሲው ከ80 እስከ 100 ሚሊዮን የሚደርስ የሕፃናት ክትባቶች ተወስደዋል። ይህም በክልሉ የሚገኙ ሕፃናት ተገቢ የክትባት አገልግሎት እንዳያገኙ አሸባሪው ቡድን ባሰማራቸው ባለሙያዎች በጥንቃቄ የተዘረፉ እና የወደመ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል አቶ እሸቴ። በኤጀንሲው ውድመት እና ዘረፋ ከተፈጸመ በኋላም የቀሩት መድኃኒቶችም በተከታታይነት ለህሙማን የሚሰጡ በመሆናቸው የሽብር ቡድኑ ወደ ውጭ በማውጣት ከጥቅም ውጭ አድርጎታል ነው ያሉት አቶ እሸቴ።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ደሴ ቅርንጫፍ በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት መድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎችን መዝረፉንና ማውደሙን አቶ እሸቴ አረጋግጠዋል። የኤጀንሲው ውድመት እና ዘረፋም በምሥራቅ አማራ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆነውን ሕዝብ ለመጉዳት ታቅዶ የተፈጸመ ወንጀል ነው፤ መንግሥት እና ሕዝቡም በወራሪው ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው-ከደሴ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
 
             
  
		