
ባሕር ዳር፡ መስከረም 24/2012 ዓ/ም (አብመድ) የሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲ፣ አቀናባሪ፣ የፒያኖና የጊታር ተጫዋቹ ኤልያስ መልካ አረፈ፡፡ የሙዚቃ ባለሙያው በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያለውና የበርካታ ደምጻውያንን ሥራ የደረሰና ያቀናበረ ነው።
ከያኒ ኤልያስ መልካ ባጋጠመው የስኳር እና ኩላሊት ሕመም ሕክምና ሲከታተል ቆይቷል፤ እስከ ባለፈው ቅዳሜ ድረስም በ‹ፋና ላምሮት የድምፀውያን ተስጥኦ ውድድር› ላይ በዳኝነት ሲያገለግል ቆይቶ ነበር።
በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ‹ቼሎ› የሙዚቃ መሣሪያን የተማረው ኤልያስ ከመምህሩ አክሊሉ ዘውዴ፣ ከእዝራ አባተ፣ ከያሬድ ተፈራና ከሌሎችም ጋር በመሆን በመዲና ባንድ ውስጥ ሠርቷል። በኋላም ከ‹ዜማ ላስታስ› እና ‹አፍሮ ሳውንድስ› የሙዚቃ ቡድኖች ጋር ሠርቷል። ከ30 በላይ ሙሉ አልበሞችንም አቀናብሯል።
ከመሐሙድ አህመድ፣ ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ቴዲ አፍሮ፣ እዮብ መኮንን፣ ሚካኤል በላይነህ፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ልዑል ኃይሉ፣ ኃይሌ ሩትስ፣ ሚካያ በኃይሉ፣ ትዕግስት በቀለ፣ ቤሪ፣ ዳን አድማሱና ሌሎችም ኤልያስ መልካ ሙዚቃ አብሯቸው የሠሩ ናቸው፡፡
ኤልያስ መልካ ዛሬ ሌሊት በመኖሪያ ቤቱ ሕይወቱ እንዳለፈ ፋብኮ ዘግቧል።
አብመድ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡