
ታኅሣሥ 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በከፈተው ጦርነት ከቀያቸው ተፈናቅለው በእብናት የመጠለያ ጣቢያ ለተጠለሉ ወገኖች ግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን መብቶች ድጋፍ አድርጓል።
ግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን መብቶች የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ነው ዛሬ ለተፈናቃዮች ያደረሰው።
በድጋፉ ላይ የተገኘው አርቲስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ በየጊዜው የሚፈናቀሉ ወገኖችን በእርዳታ ብቻ ማኖር ስለማይቻል ዘለቄታዊ መፍትሔ ያስፈልጋል ብሏል። ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅና ዜጎችን በዘላቂነት በሰላም እንዲኖሩ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል።
በግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን መብቶች በኢትዮጵያ አስተባባሪ መስዑድ ገበየሁ 400 ኩንታል ዱቄት፣ 800 ፍራሽና 750 ብርድ ልብስ በእብናት መጠለያ ጣቢያ ለተጠለሉ ወገኖች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ወደየ አካባቢያቸው እስኪመለሱ ረጅ ድርጅቶች ከጎናቸው እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
ግሎባል አሊያንስ ለኢትዮጵያውያን መብቶች በሽብር ቡድኑ ከቀያቸው ተፈናቅለው በደባርቅ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች የዕለት ምግብ እና ምግብ ነክ የልሆኑ ቁሳቁሶች እርዳታ እንደሚያቀርብ ገልጿል።
ዘጋቢ:- አስፋው ሙቀት – ከእብናት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
