“የመገናኛ ብዙኃንን ጥፋት በዝምታ ማለፉ ተገቢ አይደለም።” አስተያዬት ሰጪዎች

114

ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2012 ዓ/ም (አብመድ) በተቀናጀ መንገድ የአማራ ሕዝብ ላይ ዘመቻ ሲደረግበት የፌዴራል መንግሥት ዝምታን መምረጡ ተገቢ አለመሆኑን የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ምሁር እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ::

የአማራ ሕዝብ አንድ ሆኖ ሠላሙን ማስጠበቅ እንዳለበትም አስተያዬት ሰጭዎቹ አሳስበዋል።

አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ‹‹የተቋቋሙበትን ዓላማና የሚዲያን ሚና ወደ ጎን በመተው የተዛባ ዘገባ በማሠራጨት በአማራ ሕዝብ ላይ ዘመቻ ከፍተውበታል›› ነው ያሉት ምሁሩ እና ነዋሪዎቹ:: ለአብነትም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከሰሞኑ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ለራሳቸው በሚመች መንገድ አድርገው መዘገባቸውን ጠቅሰዋል።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ጋሻው አይፈራም እንዳሉት መገናኛ ብዙኃኑ ሕገ ወጥ እና የተዛቡ ዘገባዎችን ሲሰሩ ሕግ አስፈፃሚው አካል በዝምታ ማለፉ ተገቢ አይደለም::

አብመድ ያነጋገራቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም ‹‹ሙያዊ መርህን ሳይሆን ግጭት መቀስቀስን ዓላማ ያደረጉ መገናኛ ብዙኃን በአማራ ሕዝብ ላይ የጥላቻ በትር ለማሳረፍ ሞክረዋል›› ነው ያሉት። በተቀናጀ መንገድ የአማራ ሕዝብ ላይ ዘመቻ ሲደረግበት የፌደራል መንግሥት ዝምታን መምረጡ ተገቢ አለመሆኑንም ተናግረዋል።

ችግሩ ከተፈጠረ በኋላም ቢሆን የፌዴራል መንግሥት፣ ብሮድካስት ባለስልጣንና የሠላም ሚኒስቴር ዝምታን መምረጣቸው ተገቢነት እንደሌለውም ነው ነዋሪዎቹ አስተያዬት የሰጡት።

‹‹አማራው አንድ ሆኖ ሠላሙን ማስጠበቅ አለበት›› ያሉት ነዋሪዎቹና ምሁሩ የክልሉ መንግሥትም የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል::

የኢፌዴሪ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999 ፈቃድ ባላቸው የመገናኛ ብዙኃን ስለሚተላለፉ ዘገባዎች በክፍል አራት ዝርዝር ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 30 (1) ላይ ‹‹ማንኛውም ለሥርጭት የሚቀርብ
ፕሮግራም የተለያዩ አመለካከቶችን በማንጸባረቅ ኅብረተሰቡን በአጠቃላይ እንዲያገለግል ሚዛናዊ መሆን አለበት›› ይላል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ ደግሞ ‹‹ማንኛውም ዜና ከአድልዖ የፀዳ ትክክኛና ሚዛናዊ መሆን አለበት›› የሚል ድንጋጌ ይዟል፡፡ ይሁን እንጅ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን የአንድ ወገን መረጃን ብቻ እየያዙ ሚዛናዊ ሳይሆኑ በመዘገብ በአማራ ሕዝብ ላይ ጥላቻ እንዲፈጠር እየሠሩ በመሆኑ ሕዝቡ ቅሬታውን እየገለጸ ነው፡፡

በብሮድካስት አገልግሎት አዋጁ አንቀጽ 30 (4/ሐ፣ መ እና ሠ) ‹‹ማንኛውም ለሥርጭት የሚቀርብ ፕሮግራም የግለሰብን፣ የብሔር ብሔረሰብን የሕዝብን ወይም የድርጅትን ሥም የሚያጠፋ ወይም በሐሰት የሚወነጅል፤ ብሔረሰብን ከብሔረሰብ የሚያጋጭ ወይም በሕዝቦች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት የሚያነሳሳ፤ ጦርነት የሚቀሰቅስ መሆን የለበትም›› ተብሎ ቢደነገግም በአማራ ሕዝብ ላይ እዚህ ሁሉ ሲፈጸሙ አስፈጻሚው አካል አዋጁን አለማስከበሩ ተገቢ አለመሆኑም ነው በአስተያዬት ሰጭዎቹ የተገለጸው፡፡

ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ

Previous articleተጠርጣሪ ሰላይ መያዙን የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
Next articleየሙዚቃ ባለሙያው ኤልያስ መልካ አረፈ፡፡