በአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በለንደን ተካሄደ፡፡

98

ታኅሣሥ 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ”ኢትዮጵያን እናድን” በሚል መሪ መልዕክት በአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በለንደን ተካሂዷል፡፡

በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢትዮጵያ ዘብ እንቁም ወይም ከ“Defend Ethiopia” ዩናይትድ ኪንግደም ግብረኃይል ጋር በጋራ በመተባበር በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት መላው ዩናይትድ ኪንግደምን የወከሉ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተዋል፡፡

በለንደን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በዝግጅቱ ላይ እንደተናገሩት ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከውጪ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበር በሀገራችን አንድነት ላይ የደቀነውን ሀገርን የማፍረስ እኩይ ተግባር ለመመከት በቁጭት ተነስተናል፤ እየተገኘ ያለው የድል መንፈስ በመሰነቅ ለተፈናቀሉ ወገኖች የድጋፍ ማሰባሰብ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ በማከናወናችን ትልቅ ኩራት ይሰማናል ብለዋል፡፡

አምባሳደር ተፈሪ “የረጅም ዘመን ታሪክና ባለጸጋ የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን እና የኦነግ ሸኔ ፊታውራሪነት የተጠነሰሰው ሴራ ከሽፏል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የሚዲያ እና የአንዳንድ መንግሥታት የሐሰት ትርክት ወርጅብኝን በኢትዮጵያዊያን ትግል ተቋቁመናል” ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በገጠማት የኅልውና አደጋ ጠላትና ወዳጆችዋን የለየችበት አጋጣሚ ነው ያሉት አምባሳደር ተፈሪ በተለይም ደግሞ አፍሪካዊያን በመላው ዓለም በተካሄደው የበቃ ወይም #NoMore ዓለም አቀፍ ትግል በመሳተፍ ላሳዩት ያልተቋረጠ ድጋፍ ሊመሰገኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር በሚደረገው ትግል በለንደን ሰላማዊ ሰልፎችን በማካሄድ የሀገራቸውን ድምጽ ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በማሰማት እንዲሁም የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ድጋፍ በማድረጋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ዘብ እንቁም ወይም “Defend Ethiopia” ዩናይትድ ኪንግደም ግብረኃይል አስተባባሪ አቶ ዘላለም ተሰማ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ወደ ጦር ግንባር በመዝመት በሰጡት አመራር እየተገኘ ላለው ድል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት የሚደረገው ድጋፍ ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በበኩላቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ከመደገፍ ባሻገር ለሀገራቸው በሚፈለጉበት መስክ ኹሉ ለመደገፍ ዝግጁ ነን ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleየአማራ ወጣቶች መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀል ጠላትን እንዲያጠፉና ሀገርን በዘላቂነት እንዲያስከብሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ጥሪ አቀረቡ፡
Next articleመካነሰላም እና ከላላ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል አገኙ።