“ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የአማራ ክልል ሕዝብ ኢንዱስትሪ አድርገን ነው የምናየው፤ ሁሉም የኔ ነው ብሎ ሊይዘው ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

172

ታኅሣሥ 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ በቻይና ባለሃብቶችና በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ባለቤትነት እየተገነባ የሚገኘውን የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የግንባታ እንቅስቃሴ ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ጨምሮ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) ተገኝተዋል።

ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) እንዳሉት በክልሉ ካሁን ቀደም የነበሩ የግንባታ ሥራዎች በአብዛኛው የተጓተቱት በሲሚንቶ እጥረት ነው፤ በዚህም መፋጠን የሚገባውን የኢኮኖሚ ልማት ወደ ኋላ እንዲዘገይ አድርጓል፤ የዚህ ፕሮጀክት መፋጠንም ይህን ችግር በመቅረፍ ወሳኝነት አለው” ብለዋል።

ፋብሪካው ብዙ ተመጋጋቢ ኢንዱስትሪዎችን አካቷል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከሲሚንቶ ባለፈ የጂፕሰም፣ የሴራሚክ፣ የግላስ ፋብሪካንም ያቀፈ በመሆኑ በርካታ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

“ኢንዱስትሪውን የአማራ ክልል ሕዝብ ኢንዱስትሪ አድርገን ነው የምናየው፤ ስለሆነም ሁሉም የኔ ነው ብሎ ሊይዘው ይገባል” ነው ያሉት።

ኢንጅነር ታከለ በማኅራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “በሁሉም ዘርፍ ሀገራዊ የምርት አቅማችንን በማሳደግ በሀገራዊ ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል መመጣጠን መፍጠር ዋነኛው ዓላማችን ነው፤ ይህን ለማድረግም በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ የማዕድን ሀብታችንን ጥቅም ላይ እንዲውል እናደርጋለን” ነው ያሉት፡፡

በምርት ላይ የሚገኙ አምራች ፋብሪካዎችን በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በማገዝ በሌላ በኩል ደግሞ አቅምና የሥራ ፍላጎት ያላቸውን አምራች ኢንዱስትሪዎችን በስፋት ወደ ኢንቨስትመንት በማስገባት እንደሚሳካም አንስተዋል።

የግንባታ እንቅስቃሴው ተጠናቆ በአፋጣኝ ወደ ምርት እንዲገባም ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ከአማራ ክልል ጋር በትብብር እንደሚሠሩም ነው ኢንጂነር ታከለ የገለጹት።

በክልሉ ያለውን የማዕድን ምርት በአፋጣኝ ወደ እንቅስቃሴ መመለስም በትኩረት የሚሠራ ቀጣይ ተግባር እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleየአማራ ባለሃብቶች ጥምረት ለሀገሩ ሕልውና ከልጁ ጋር በክብር ለተሰዋው አቶ እሸቴ ሞገስ ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡
Next articleየ”በቃ” ንቅናቄ በአውስትራሊያ ሜልቦርን ተካሄደ